መምህራኑ የእጅ ንጽህና መጠበቂያ አመረቱ

59

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 14/2012 (ኢዜአ) በአዲስ አበበ ከተማ የፌታውራሪ ላቀ አድገህ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሳይንስ መምህራን የኮሮና ተህዋሲን ለመከላከል የእጅ ንጽህና መጠበቂያ (ሳኒታይዘር) አመረቱ።

በትምህርት ቤት ደረጃ ሳኒታይዘር ሲመረት ''የመጀመሪያው'' ነው ተብሏል።

የከተማ አስተዳደሩ ትምህርት ቢሮ በትምህርት ቤቶች ከአሁን በፊት ከቤተ ሙከራ የማያልፈው ምርምር ለአገልግሎት የሚውል ምርት ማስገኘቱ የፈጠራ ተነሳሽነትን ይፈጥራል ብሏል።

በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 በሚገኘው ትምህርት ቤት መምህራን ወደ ምርት የገቡት ማህበረሰባዊ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት እንደሆነም ተገልጿል።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ተሾመ "የሳኒታይዘር ምርት በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሲሰራ የመጀመሪያው" መሆኑን ገልጸዋል።

በአገሪቷ የተከሰተውን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በጋራ ለመከላከል መምህራኑ የቀለም ትምህርትን ወደ ተግባር በመቀየር ያሳዩት እንቅስቃሴ ተማሪዎችን የሚያነቃቃና የሚያነሳሳ ነው ብለዋል።

ሌሎች ትምህርት ቤቶችም ተሞክሮውን በመውሰድ እንዲንቀሳቀሱ ምክትል ኃላፊው አሳስበዋል።

ቢሮው በምርምር ለሚሳተፉ ትምህርት ቤቶች ግብዓቶችን ለማሟላትና ለማገዝ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።

በምርምሩ የተሳተፉት መምህር ምህረት ነጋው በተሰማሩበት የትምህርት ዘርፍ ወረርሽኙን ለመመከት ከባልደረቦቻቸው ጋር ተመካክረው ወደ ሥራ መግባታቸውን ተናግረዋል።

ምርቱን 99 ነጥብ 9 በመቶ ውጤት በማግኘት ብቃቱ አግባብ ባለው አካል መረጋገጡን ገልጸዋል።

የትምህርት ቤቱ ምክትል ርዕሰ መምህር ዘውዱ ጌታቸው በበኩላቸው ምርቱ በክፍለ ከተማው ገቢያቸው አነስተኛ ለሆነ የኅብረተሰብ ክፍሎች በነጻ እንደሚከፋፈል ገልጸዋል።

የክፍለ ከተማው ምግብ፤ መድኃኒት ጤና ክብካቤ አስተዳደር ቁጥጥር ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሪት ሐረገወይን ኪዳነማርያም "ምርቱ ሂደቱን በጠበቀ መንገድ ተፈትሾ 99 ነጥብ 9 በመቶ ውጤታማ ነው'' ብለዋል።

መምህራኑ ደረጃውን የጠበቀ ምርት በማምረት ለማህበረሰቡ ተደራሽ ለማድረግ ያሳዩትን ተነሳሽነትም አድንቀዋል።

በኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን ኅብረተሰቡ ሳይመዘገቡና የብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ ሳያገኙ በሕገ-ወጥ መልክ የእጅ ንጽህና መጠበቂያ አምርተው ለገበያ የሚያቀርቡ ግለሰቦችና ተቋማት ጥንቃቄ እንዲያደርግ ማሳሰቡ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም