በአዲስ አበባ የላምበረት አከባቢ ወጣቶች ለአቅመ ደካሞች ከ700 ሺህ ብር በላይ ግምት ያለው የቁሳቁስ ድጋፍ አደረጉ

128

አዲስ አበባ፣ ሰኔ14/2012(ኢዜአ) በአዲስ አበባ የላምበረት አካባቢ ወጣቶች ለአቅመ ደካሞች ከ700 ሺህ ብር በላይ ግምት ያለው የምግብና የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን ድጋፍ አደረጉ።

ከድጋፍ አስተባባሪዎቹ መካከል ወጣት ደስታ ጌታቸው መንግስት ያቀረበውን የማእድ ማጋራት ጥሪ በመቀበል የተቻላቸውን ለማድረግ መነሳሳታቸውን ተናግሯል።

በመሆኑም በየካ ክፍለ ከተማ ላምበረትና አካባቢው የሚኖሩ አቅመ ደካማና ችግረኛ የሆኑ 300 ዜጎችን በመለየት ድጋፍ መደረጉን ገልጿል። 

ወጣቶቹ በሀገር ውስጥ እና በውጭ ከሚኖሩ ዜጎች ያሰባሰቡትን ከ700 ሺህ ብር በላይ የምግብና የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን በመሸመት በዛሬው እለት አበርክተዋል።

በድጋፉ ዱቄት፣ ሩዝ፣ ፓስታ መኮረኒ እና ሌሎችም የምግብ ቁሳቁሶችን ጨምሮ ሳሙና፣ ሳኒታይዘርና የንፅህና መጠበቂያ አልኮልም ለግሰዋል።

የመርሃ ግብሩ አላማም የኮቪድ -19 ወረርሽኝ ሊያመጣ የመችለውን ኢኮኖሚያዊ ተጽእኖ ለመቀነስ ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ወጣቶቹ ገልጸውልናል።

የየካ ክፍለ ከተማ ዋና ስራአስፈጻሚ አቶ አስፋው ለገሰ እንዳሉት በክረምቱ የተለያዩ በጎ ተግባራትን ለማከናወን ዝግጅት ተደርጓል።

በክረምቱ በክፍለ ከተማው የ140 አቅመ ደካማ ዜጎችን ቤት ለማደስ እቅድ መያዙንም ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ በዘንድሮው ክረምት የተለያዩ በጎ ተግባራትን ለማከናወን ከ1 ሚሊዮን በላይ ወጣቶች ዝግጁ ሆነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም