የኢትዮጵያን የብልፅግና ጉዞ ለማረጋገጥ የአረንጓዴ አሻራ ሁነኛ መሣሪያ ነው -- ሚኒስትር ሙፈሪያት

101

አዲስ አበባ ሰኔ 13/2012(ኢዜአ) የኢትዮጵያን የብልፅግና ጉዞ ለማረጋገጥ የአረንጓዴ አሻራ ሁነኛ መሣሪያ መሆኑን የሠላም ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል ተናገሩ፡፡ 

ሚኒስትሯ በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 06 የአዋሬ አካባቢ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ሲያካሂዱ ተገኝተው መልዕክት አስተላልፈዋል።

በችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የብልፅግና ፓርቲ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ በልጅጌ እና የትግራይ ቅርንጫፍ ብልፅግና ፓርቲ ኃላፊ አቶ ነብዩ ስሁል ተሳትፈዋል።

ወይዘሮ ሙፈሪያት ለአረንጓዴ ልማት ትኩረት መስጠት የለማና የበለፀገ አስተሳሰብ ያለው ትውልድ አዕምሮ ውጤት መኖር ማሳያ ነው ብለዋል በንግግራቸው።

የኢትዮጵያን የብልፅግና ጉዞ ለማረጋገጥም የአረንጓዴ አሻራ ሁነኛ መሳሪያ እንደሆነም አክለዋል።

ወጣቱ አገሩን ለነገው ትውልድ እየሰራ ነው ያሉት ወይዘሮ ሙፈሪያት ይህን በበለፀገ አስተሳሰብ የለማ አካባቢ ለቀጣዩ ትውልድ በማውረስ ኢትዮጵያን ለማሻገር መሰረት እንደሚሆን ተናግረዋል።

የአረንጓዴ ልማትን የሚያረጋግጥ ትውልድ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቆጣጠር የሚደረገውን ጥረት ከማገዝ ባሻገር ወጣቱ ራሱን የሚያዳምጥበት፣ ዓይኑ የሚያርፍበት፣ መንፈሱ የሚረካበትና የጥሞና ጊዜውን በመልካም የሚያሳልፍበትን ቦታ ለመፍጠር እንደሚያግዝ ገልፀዋል።

የአዲስ አበባ አስተዳደር የብልፅግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋዬ በልጅጌም መላውን ዓለም ስጋት ውስጥ የከተተውን የአየር ንብረት ለውጥና ሙቀት መጨመር ለመቀነስ፣ ለመቆጣጠርና ለመካላከል ብሎም ኢትዮጵያ ወደ ብልጽግና የምታደርገውን ጉዞ ለማረጋገጥ ዋነኛው መሳሪያ ችግኝ ተክሎና ተንከባክቦ ማሳደግ እንደሆነ ገልጸዋል።

የከተማ አስተዳደሩ የብልጽግና ፓርቲ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመቆጣጠር ከሚያደርገው ሰፊ እንቅስቃሴ ጎን ለጎን በከተማ ደረጃ ሰባት ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል የተያዘው ዕቅድ ግቡን እንዲመታ የከተማዋን ወጣት በበጎ ፈቃደኝነት በማሳተፍ እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

አገር የምትገነባው በእያንዳንዱ ዜጋ በጎ ተሳትፎ ነው ያሉት አቶ ተስፋዬ ወጣቱም እምቅ አቅሙን በልማት ስራዎች ለአገር ብልጽግናና ግንባታ ማዋል እንደሚገባው አሳስበዋል።

የየካ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አስፋ ለገሰ በበኩላቸው ለቀጣዩ ትውልድ የተሻለች ኢትዮጵያን ለማሻገር አረንጓዴ አሻራውን ማሳረፍ የሚችል አስደማሚ ትውልድ ማፍራት ተችሏል ነው ያሉት።

ከአካባቢው በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በተጨማሪ የፌዴራልና የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ችግኝ በመትከል የአረንጓዴ አሻራቸውን አሳርፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም