በመሰረተ ልማት ዙሪያ ከኢትዮጵያ ልምድ ሊወሰድ ይገባል...ሌፍተናንት ጀኔራል መሐመድ ሐምዳን ዳግሎ

ሰኔ 13/2012(ኢዜአ) ሱዳን በመንገድ ፣ በባቡር ሃዲድ እንዲሁም በአግሮ ፕሮሰሲንግ እና በከተሞች ልማት ከኢትዮጵያ ልምድ ሊትወስድ እንደሚገባ የሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤት ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት ገለጹ፡፡

የሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤት ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት ሌፍተናንት ጀኔራል መሐመድ ሐምዳን ዳግሎ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ጋባዥነት በኢትዮጵያ ለሶስት ቀናት ይፋዊ ጉብኝት አድርገው ዛሬ ከሰአት በኋላ ወደ ካርቱም ተመልሰዋል፡፡

ዳግሎ ወደ ሀገራቸው ከተመለሱ በኋላ እንዳሉት በኢትዮጵያ ባደረግኩት ጉብኝት ሱዳን በመሰረተ ልማት ዙሪያ በዋናነት በመንገድ ፣ በባቡር ሃዲድ እንዲሁም በአግሮ ፕሮሰሲንግ እና በከተሞች ልማት ልምድ ሊትወስድ ይገባል ብለዋል።

የሉዓላዊ ምክር ቤቱ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት ሌፍተናንት ጀኔራል መሐመድ ሐምዳን ዳግሎ ሀገራቸው ከተመለሱ በኋላ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በድንበር ፣ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፣ በሱዳንና ደቡብ ሱዳን ሰላም ጉዳይ እንዲሁም በአብዬ ግዛት ጉዳዮች ላይ ውጤታማ ውይይት ማድርጋቸውን አብራርተዋል፡፡

ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ጋር በባቡር ሐዲድ ዙሪያም መነጋገራቸውን ያነሱት ዳግሎ፤ በባቡር መስመር ፖርት ሱዳንን እና ካሮቱምን ከኢትዮጵያ ጋር ለማገናኘት የሚያስችል ፕሮጀክት ላይም መምከራቸውን አንስተዋል ፡፡

ሌፍተናንት ጀኔራል መሐመድ ሐምዳን ዳግሎ ካርቱም አየር ማረፊያ ስደርሱም በሽግግር ምክር ቤቱ አባላት አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡

የሉዓላዊ ምክር ቤት ዋና ፀሀፊ ሌፍተናንት ጀኔራል ኢብራሂም ጃቤር ፣ ሌፍተናንት ጀኔራል መሀመድ አል-ጋሊ አሊ ዩሱፍ እና የመንግስት ባለስልጣናት አቀባበል አድርገውላቸዋል።

ሐምዳን ዳግሎ ወጣት የሱዳናዊያን ነጋዴዎችም ከኢትዮጵያ ተሞክሮ በመውሰድ በንግድና ኢኮኖሚ ዘርፍ ተጠቃሚ እንዲሆኑም ጥሪ ማቅረባቸውን አልንቲባሃ የተባለ ጋዜጣ ዘግቧል።

የሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤት ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንቱ በኢትዮጵያ በነበራቸው ቆይታ በአዲስ አባበ እየተሰሩ ያሉ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች፣ የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክና ሌሎች ፕሮጀክቶችን መጎብኘታቸው ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም