በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ በጎ ተግባር በማከናወን ታሪክ መስራት እንደሚቻል ማሳያ ሊሆን ይገባል

118

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 13/2012 ( ኢዜአ) በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ ኢትዮጵያውያን በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ በጎ ተግባር በማከናወን ታሪክ መስራት እንደሚችሉ ማሳያ ሊያደርጉት ይገባል ሲሉ በጎ ፈቃደኞች ገለጹ።

"ላቭ ኤንድ ኬር" የተሰኘ የበጎ ፈቃደኞች ማህበር በአዲስ አበባ ሲ ኤም ሲ አካባቢ የአረንጓዴ አሻራ አካል የሆነውን ችግኝ የመትከል ስነ-ስርዓት አካሂደዋል።

በጎ ፈቃደኞቹ ''የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝ ለደቀነው ፈተና እጅ ሳንሰጥና ጥንቃቄ በማድረግ የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻን እውን ለማድረግ በበጎነት እንነሳ'' ሲሉ ጠይቀዋል።

ወጣት ሩት ሃይሉ የዘንድሮው አረንጓዴ አሻራ ዘመቻ የተለየ ትርጉም እንደሚሰጣት ገልጻለች።

አለም በኮቪድ-19 ወረርሽኝ እየተፈተነች ባለችበት ወቅት 5 ቢሊዮን ችግኝ በመትከል አረንጓዴ አሻራን ለማሳረፍ መነሳት አገራዊ ጥንካሬን የሚያሳይ መሆኑን ጠቅሳለች።

ኢትዮጵያውያን በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆነው ታሪክ በመስራት ለትውልድ ማስተላለፍ እንደሚችሉ ማሳያ እንደሚሆንም እምነቷን ገልጻለች።

ወጧቷ ዶክተር ውብእርስት ተስፋዬ በበኩሏ ተፈጥሮ ከሰው ልጅ ጋር ያለውን ቁርኝት በማብራራት፤ ''ተፈጥሮ ሲዛባ የመኖር ህልውና አደጋ ውስጥ ይገባል'' ብላለች።

በመሆኑም የተፈጥሮን ሚዛን ለማስቀጠል ዘመቻ ሳይጠብቅ እያንዳንዱ ሰው ችግኝ በመትከል ሊንከባከብ እንደሚገባ አስገንዝባለች።

ሌላው በጎ ፈቃደኛ ወጣት ቢኒያም ስለሺ "ወጣቶች በችግኝ መትከል ዘመቻው በመሳተፍ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ታሪክ መስራት እንደሚቻል ለቀጣዩ ትውልድ ምሳሌ መሆን አለባቸው" ሲል ገልጿል።

ከሌሎች የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች ጎን ለጎን አረንጓዴ አሻራ ያለውን አገራዊ ጠቀሜታ በመረዳት ችግኝ መትከሉን ገልጿል።

አገራዊውን የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ በመቀበል ከ150 በላይ በጎ ፈቃኞችን በማስተባበር ችግኝ መትከላቸውን የተናገሩት ደግሞ የቡድኑ አስተባባሪ ወይዘሮ ራሄል አሸብር ናቸው።

ለኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በማያጋልጥ መልኩ ርቀትን በመጠበቅና ጥንቃቄ በማድረግ ሁሉም ችግኝ በመትከል በጎ ተግባር ማከናወን እንደሚችል በጎ ፈቃደኞቹ መክረዋል።

"ላቭ ኤንድ ኬር" የበጎ ፈቃደኞች ማህበር ከስምንት አመት በፊት የተመሰረተ ሲሆን ትኩረቱን በህጻናት ላይ በማድረግ የሚሰራና ከ400 በላይ አባላት ያሉት ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም