ባህርዳርና ፋሲል ከነማ የ6 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ተደረገላቸው

444

ባህርድር ሰኔ 13/2012(ኢዜአ) የአማራ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ባህርዳርና ፋሲል ከነማ እግር ኳስ ክለቦች የገጠማቸውን የገንዘብ እጥረት ለማገዝ የስድስት ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን አስታወቀ። 

የፓርቲው ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አገኘሁ ተሻገር በባህር ዳር ከተማ ማምሻውን ገንዘቡን ባስረከቡበት ወቅት እንዳሉት ድጋፉ ክለቦቹ በኮሮና መከሰት ምክንያት የገጠማቸውን የፋይናንስ እጥረት ለማገዝ ታስቦ የተደረገ ነው።

“ክለቦቹ በእግር ኳሱ ዘርፍ ጠንክረው በመስራት ሀገራቸውንና የክልላቸውን ስም እንዲያስጠሩ የፋይናንስ ችግራቸው እስኪፈታም የክልሉ መንግስትና ፓርቲው ድጋፍ ያደረጋል”ብለዋል።

በቀጣይም የራሳቸው ቋሚ የገቢ ማስገኛ እንዲኖራቸውና ከጥገኝነት ተላቀው እንዲቀጥሉ አስፈላጊውን ዕገዛ እንደሚደረግም ገልፀዋል።

ባለሃብቶች፣ የንግዱ ማህበረሰብ፣ ተቋማትና ግለሰቦች ክለቦቹን ለማጠናከር በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል።

የአማራ ክልል ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ባዘዘው ጫኔ በበኩላቸው ክለቦቹ የገጠማቸውን የፋይናንስ እጥረት ለማቃለል ፓርቲው ያደረገው የገንዘብ ድጋፍ ለስፖርት ያለውን ፅኑ ፍላጎት የሚያሳይ ነው።

“ክለቦቹ የክልሉ ብቻ ሳይሆኑ የሀገሪቱም ሃብቶች በመሆናቸው ጠንክረው በመስራት ሀገራቸውንና ክልላቸውን በእግር ኳሱ ዘርፍ ወደ ተሻለ ደረጃ እንዲያሳድጉ መስራት አለባቸው” ብለዋል።

ክለቡ ቋሚ የገቢ ማስገኛና የራሱ ካምፕ ስለሌለው ከተከሰተው የኮሮና ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ የገንዘብ እጥረት እንደገጠመው የተናገሩት ደግሞ የባህርዳር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የባህርዳር ከነማ ፕሬዝዳንት አቶ አማረ አለሙ ናቸው። 

ከከተማ አስተዳደሩ ከተመደበለት 20 ሚሊዮን ብር በተጨማሪ ከህብረተሰቡና ከደጋፊ ማህበሩ በሚሰበሰብ ገንዘብ ወጪውን እንደሚሸፍንም አስረድተዋል። 

የፋሲል ከነማ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አብወት ብርሃኑ በበኩላቸው “በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ለክለቡ የተደረገው ድጋፍ ወቅታዊ ችግሩን በጊዜያዊነት እንዲቋቋም ያግዘዋል”ብለዋል።

በቀጣይም የክለቡ እጣ ፈንታ አስቸጋሪ ሊሆን ስለሚችል የክልሉ መንግስት ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የሚቻልባቸውን መንገዶች እንዲያምቻችም ጠይቀዋል።

በድጋፍ አሰጣጡ ስነ-ስርዓትም የክልሉ ከፍተኛ አመራሮችና የክለቡ ቦርድ ሰብሳቢዎች እንዲሁም አባላት ተገኝተዋል።