በደቡብ ክልል ኮሮናን ለመከላከል የሚደረገው ጥረት ወጥነት ይጎለዋል–የክልሉ ምክር ቤት አባላት

228

ሐዋሳ፣ ሰኔ 13/2012 (ኢዜአ) በደቡብ ክልል የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል እየተደረገ ያለው ጥረት ወጥነት ስለሚጎድለው ሊስተካከል እንደሚገባ የክልሉ ምክር ቤት አባላት አሳሰቡ።

የክልሉ ምክር ቤት በሀዋሳ ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን መከላከልና የቁጥጥር ሥራዎች አፈጻጸም ሪፖርት አዳምጧል።

በዚህ ጊዜ የጉባዔው  አባላት እንዳሉት በክልሉ የሻካ ፣ካፋና ደቡብ ኦሞ ዞኖች የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል በመንግስት ደረጃ እየተወሰዱ ያሉ ጥረቶች አፈጻጸምና የመመርመሪያ መሳሪያዎች ስርጭት ወጥነት ይጎለዋል ብለዋል ።

የምክር ቤቱ አባል አቶ ጸጋዬ ማሞ እንደገለጹት የኮሮና ቫይረስ እያስከተለ ካለው ዘርፈ ብዙ ጫና ለመውጣት የሚያስችል የአስተሳሰብ ለውጥ ለማምጣት የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል አለበት።

በተለይ በገጠር የሃገሪቱ ክፍሎችና በገበያ ስፍራዎች የሚስተዋለው ጥንቃቄ የጎደለው ጥግግት ለማረም የሚወሰዱ እርምጃዎች የሰው ህይወት ለመታደግ በሚያስችል መልኩ ወጥነት ሊኖራቸው ይገባል ብለዋል።

ወደ ምዕራቡ የደቡብ ክልል የቫይረሱ የመመርመሪያ ማዕከል አለመኖሩ ስርጭቱን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት የሚያዳክም በመሆኑ ክልሉ የማስተካከያ እርምጃ ሊወስድ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ከደቡብ ኦሞ ዳሰነች ወረዳ የመጡት የምክር ቤት አባል ወይዘሮ ናኪያ አነቆሲያ በበኩላቸው በክልሉ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ለመከላከል እየተደረገ ባለው ጥረት የአፈጻጸም ወጥነት አለመኖሩን ተናግረዋል።

ለአብነት ሞተር ሳይክሎች ከአንድ ሰው በላይ በመጫን ከአስቸኳይ አዋጁ ባፈነገጠ መልኩ አገልግሎት ሲሰጡ ይታያል ብለዋል።

የከፋ ዞን ተወካይ ወይዘሮ አሰገደች ሃይሌ  በበኩላቸው የኮሮና ቫይረስ መመርመሪያ ማሽንና ማዕከል በአካባቢው ከአለመኖሩ የተነሳ ወላይታና ሃዋሳ ድረስ ናሙናው እንደሚላክ ገልጸዋል።

ይህም ለከፍተኛ እንግልት የሚዳርግ መሆኑን ገልጸው ቫይረሱን ለመከላከል እየተደረገ ያለውን ጥረት እየጎዳ መሆኑን አንስተዋል።

የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው በሰጡት ምላሽ መንግስት ከሁሉም በላይ የህዝብን ደህንነት ለማረጋገጥና  የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የሚያስችሉ ተግባራት ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ነው።

ይሁን እንጂ በገበያ ስፍራዎች ፣ በሃይማኖት ተቋማት እንዲሁም በትራንስፖርት አካባቢ የሚስተዋለው መዘናጋት ዋጋ እንዳያስከፍል ማህበረሰቡ የባህሪ ለውጥ ማምጣት ይገባል ብለዋል።

የመመርመሪያ ማሽን ስርጭት በተመለከተም ምርመራ የጀመሩ ተቋማት ቀድሞ የነበራቸው ማሽን እንጂ ክልሉ አዲስ የመመርመሪያ ማሽን ለማንም አለመስጠቱንና ከፍትሃዊነት ጋር መያያዝ እንደሌለበት አስረድተዋል።

የክልሉ መንግስት በክልሉ ስራ ላይ ያሉትን ጨምሮ ስምንት ማዕከላትን ለመክፈት በቂ በጀት መድቦና አቅዶ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸው፤ በገበያ የመመርመሪያ ማሽን አቅርቦት እጥረት ችግር መፈጠሩን ጠቅሰዋል።

ይህን ክፉ ጊዜ በአንድነት፣በመተጋገዝና በመተባበር ማለፍ ተገቢ መሆኑን የገለጹት አቶ ርስቱ የተጀመረው ማዕድ የመጋራትና አቅመ ደካሞችን የመደገፍ ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።