የትግራይ ህዝብም ይሁን በህወኃት ውስጥ ያሉ አዳዲስ አመራሮች ህዝብንና ሃገርን የሚጎዱ የፖለቲካ ውሳኔዎችን ታግለው ማስተካከል አለባቸው...አቶ ከበደ ጫኔ

212

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 12/2012(ኢዜአ) የትግራይ ህዝብም ይሁን በህወኃት ውስጥ ያሉ አዳዲስ አመራሮች ህዝብንና ሃገርን የሚጎዱ የፖለቲካ ውሳኔዎችን ታግለው ማስተካከል እንዳለባቸው የቀድሞው የብአዴን ኢህአዴግ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አቶ ከበደ ጫኔ ተናገሩ።

የክልሉ ህዝብ በመሪ ድርጅቱ አስተሳሰብ ተፅዕኖ ብቻ ለማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ስነ ልቦናዊ የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ መግባት የለበትም ሲሉም ተናግረዋል።

የደርግን መንግስት ለመጣል በተደረገው ትግል ተሳታፊ የነበሩትና የቀድሞው የብአዴን ኢህአዴግ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አቶ ከበደ ጫኔ ከኢዜአ ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ቆይታ አድርገዋል።

በክልሉ መሪ ፓርቲ ህወኃት እየተራመዱ ያሉ ምርጫ የማካሄድ፣የመገንጠልና መሰል የፖለቲካ አቋሞች ለትግራይም ለሌሎች የኢትዮጵያ ህዝብም የሚጠቅም አይደለም ሲሉም ተናግረዋል።

ህወሃት ከሚያደርጋቸው የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ውስጥ በተለይ ለተባበሩት መንግስታትና ለሌሎች አለም አቀፍ ድርጅቶች የሚፃፉ ደብዳቤዎች ህዝብን እየመራ ያለውን መንግስት ከማጥላላት በዘለለ የሚያመጡት ፖለቲካዊ ለውጥ አይኖርም ሲሉም ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪ በኮቪድ 19 መከሰት ምክንያት የህገ መንግስት ትርጉም ተደርጎ ምርጫ መራዘሙ ህዝብን የሚያድን ሆኖ ሳለ ምርጫ እናካሂዳለን ፣የራሳችንን ሃገር እንመሰርታለን የሚሉ የፖለቲካ አቋሞችን ህወሃት ቆም ብሎ ሊያስብባቸው ይገባልም ብለዋል።

በተለይም መገንጠል የሚለው ሃሳብ መነሳት የሌለበት ነው ያሉት አቶ ከበደ፤ ይህም ከሆነ ብዙ ህገ መንግስታዊና ህጋዊ አሰራሮችን ጨምሮ የህዝብን ይሁንታ የሚጠይቅ እንጂ አንድ ፓርቲ ሊወስነው አይችልምም ብለዋል።

አሁን በትግራይ ክልል መሪ የፖለቲካ ድርጅት ህወሃት የተያዘው አቋም የትግራይ ህዝብ ከኢትይጵያዊነቱ የሚያገኛቸውን ጥቅሞች የሚያስቀር፣እስከ መገንጠል የሚያደርስና የህዝብ ፍላጎትን መሰረት ያላደረገ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

ህዝብን መሰረት ሳያደርግ በጥቂት መሪዎች ፍላጎት ብቻ የትግራይን ህዝብ አጣብቂኝ ውስጥ መክተት ተገቢ ባለመሆኑ ቆም ብለው ሊመለከቱት ይገባልም ሲሉ  ነው አቶ ከበደ የተናገሩት።

አቶ ከበደ ""ህወሃት ለውጥን የሚፈልግ አዲስ ሃይልና የተበላሸ የቆዬ የፖለቲካ ሃይል ቅልቅል ባህሪን እያሳዬ ነው" ሲሉም ተናግረዋል።

ይህን የፖለቲካ አካሄድ ለመቀየር በህወሃትና በብልፅግና ፓርቲ በኩል ውይይት ማካሄድና ልዩነታቸውን ማጥበብ ቀዳሚ ተግባር መሆኑንም ጠቅሰው፤ ይህ ካልሆነ ግን በመጀመሪያ ህዝቡ ለመብቱ መታገል አለበት፣ሁለተኛ በውስጡ ያለው አዲስ አመራር የተበላሸውን የፖለቲካ አካሄድ ቀይሮ ድርጅቱንም ህዝቡንም መታደግ ይጠበቅበታል ሲሉም ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም