ግብረ ኃይሉ የቫይረሱን ተጋላጭነት ለመቀነስ ድንበር ተሸጋሪ አሽከርካሪዎች እንዲጠነቀቁ አሳሰበ

103

አፋር፣ ሰኔ12/2012(ኢዜአ) በአፋር ክልል የኮሮና ቫይረስ ተጋላጭነት ለመቀነስ ድንበር ተሸጋሪ አሽከርካሪዎች ተገቢው ን ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባ የክልሉ ኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል አሳሰበ።

የግብረ ኃይሉ አባልና የክልሉ  ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ያሲን ሀቢብ እንደገለጹት  በክልሉ ቫይረሱን  የመከላከል ስራዎች በበመንግስታዊ ባለድር አካላትና ህብረተሰቡ ተሳትፎ  ተጠናክሮ ቀጥሏል። 

በተለይም ክልሉ ከጁቡቱና ኤርትራ ጋር የሚዋሰን ከመሆኑም በላፈ የድንበር ተሸጋሪ አሽከርካሪዎች የሚያልፉበት ሰፊ የትራንስፖርት ኮሪደር ነው።

በዚህም የቫይረሱ ተጋላጭነት ስጋት  እንደለ  ጠቁመዋል።

የክልሉ መንግስት ከፌዴራል ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ደንበር ተሻጋሪ አሽከርካሪዎች በጂቡቱ የሚኖራቸውን ቆይታ  ለማሳጠር በዲችኦቶ ከተማ የጭነት ተሽከርካሪዎች ማስተናገጃ ተርሚናል ግንባታ እየተፋጠነ መሆኑን  ተናግረዋል።

ወረርሽኙ  እየጨመረ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ  በየዞን  የህክምናና  በሁሉም ወረዳዎች የለይቶ ማቆያ ማዕከላት  በማደራጀት  ቫይረሱን ለመከላከል የተሻለ አቅም  ተፈጥሯል ብለዋል።

በተለይም የኢትዮ-ጂቡቲ የትራንስፖርት  ኮሪደርን ተከትለው  ተጋላጭ ናቸው ተብለው በተለዩ ሆቴሎች ነዳጅ ማደያዎችና ተያያዥ አካባቢዎች ላይ ያተኮረ የቤት ለቤት የቅኝት ስራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውንም ጠቅሰዋል።

ሆኖም  መንግስት በሽታውን ለመከላከል ከሚያደርገው  ጥረት በተጓዳኝ ተጋላጭነትን ለመቀነስ  ድንበር ተሸጋሪ አሸከርካሪዎች የዕለት ተዕለት  እንቅስቃሴያቸው በጥንቃቄ ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል።

ይህም ለራሳቸው፣  ለቤተሰባቸውና ለሌላውንም ማህበረሰብ ደህንነት ኃላፊነት ስላለባቸው መሆኑን ጠቁመዋል።

የአፋዴራ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኡመር ሁመድ በበኩላቸው   ወደ አካባቢው ጨው ለመጫን በቀን ከ60 በላይ ተሽከርካሪዎች የሚገቡበትና የሚወጡበት ሁኔታ እንዳለ ተናግረዋል።

እነዚህ ተሽከርካሪዎች   ጨው ለመጫን  ወረፋ እስከሚደርሳቸው  ከከተማ ውጭ እንዲቆዩ ከማድርግ ባለፈ የኬሚካል ርጭት እየተደረገባቸው ነው ብለዋል።

በተጨማሪም አሽከርካሪዎች  ለጥንቃቄ የራሳቸው ጊዜያዊ የማረፊያ በማዘጋጀትና  ሌሎች የሚያስፈልጋቸውን  ባሉበት በማመቻቸት ቫይረሱን ለመከላከል ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም