በአዲስ አበባ ለሁሉም የመንግስት ትምህርት ቤት ተማሪዎች የተሟላ የደንብ ልብስ በነፃ ይቀርባል

134

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 12/2012 (ኢዜአ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሚቀጥለው የትምህርት ዘመን ለሁሉም የመንግስት ትምህርት ቤት ተማሪዎች የተሟላ የደንብ ልብስ በነፃ እንደሚቀርብ ገልጿል፡፡ ከደንብ ልብስ በተጨማሪ ጫማና ቦርሳም ለተማሪዎቹ በነፃ ይቀርብላቸዋል ተብሏል።

የከተማ አስተዳደሩ ለመንግስት ትምህርት ቤት ተማሪዎች የሚውሉ አራት አይነት የደንብ ልብሶችን አስመርቋል።

የደንብ ልብሶቹ ለመዋለ ህፃናት፣ ከ1-6፣ ከ7-8 እና ከ9-12 ባሉ የትምህርት ደረጃዎች የተመደቡ ናቸው፡፡

አስተዳደሩ በመንግስት ትምህርት ቤት ለተመዘገቡት 600 ሺህ ተማሪዎች ከደንብ ልብስ ባሻገር ጫማና ቦርሳን ያቀርባል።

ከተማሪዎቹ መካከል ከ380 ሺህ በላይ የሚሆኑት ደግሞ በምገባ መርሃ ግብር እንደሚካተቱ ተገልጿል፡፡

በበይነ መረብ በተደረገ የደንብ ልብስ መረጣ መርሃ ግብር ላይ ተማሪዎች፣ የተማሪ ወላጆችና የስነ-ልቦና ባለሙያዎች መሳተፋቸው ተገልጿል፡፡

የአስተዳደሩ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ወይዘሪት ፌቨን ተሾመ፣ ለ2013 የትምህርት ዘመን ለተማሪዎቹ ከደንብ ልብስ፣ የትምህርት ቁሳቁስ እና ምገባ አቅርቦት በተጨማሪ ጫማና ቦርሳ እንደሚሰጣቸው ገልጸዋል፡፡

በመጪው የትምህርት ዘመን ለተማሪዎች የሚሰጡ አገልግሎቶች በመጠን፣ በጥራት እና በአይነት በተሻለ መልኩ ተደራሽ እንደሚሆኑም ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ወይዘሮ አበበች ነጋሽ በበኩላቸው የከተማ አስተዳደሩ ባለፈው ዓመት የአልባሳት፣ የምገባ እና የትምህርት ቁሳቁሶችን ማቅረቡን አስታውሰዋል።

አሁንም ይሄው መልካም ጅማሮ ዘንድሮም ጫማና የደብተርና መፅሃፍት መያዣ ቦርሳን ጭምር ለማቅረብ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።

አቅርቦቱ ቀጣይነት እንዲኖረው ለማድረግ የአስተዳደሩ ምክር ቤት የተማሪዎች ምገባ ኤጀንሲን በአዋጅ አቋቁሟልም ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ የተማሪዎች ምገባ ኤጀንሲ ኃላፊ ወይዘሮ አንችነሽ ተስፋዬ እንዳሉት የከተማ አስተዳደሩ በሰጠው ትኩረት የተማሪዎች አገልግሎት አቅርቦት ሁሉንም ያካተተ እና አሳታፊ አንዲሆን ተቋማዊ ስርዓት ተዘርግቷል፡፡

ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆኑ ዜጎች የተማሪዎች አገልግሎት አቅርቦት የህብረተሰቡ ዋነኛ ጉዳይ እንዲሆን ሙያቸውን በመጠቀም አጋርነታቸውን ማሳየት እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡

ምግብ የሚያዘጋጁ እናቶችም የምግብ ዝግጅት ስልጠና ወስደው ወደ ስራ እንደሚገቡ ተነግሯል፡፡

በተመረጡ ትምህርት ቤቶች ላይ ተማሪዎችን በማሳተፍ የከተማ ግብርና በመተግበር ምርቱ ለትምህርት ቤቶቹ የምገባ አገልግሎት እንደሚውል ተነግሯል፡፡

በስነ-ስርዓቱ ላይ የተማሪ ምግብ የሚያዘጋጁ እናቶች እና የመምህራን የደንብ ልብሶችም ለእይታ ቀርበዋል፡፡

ከመርሃ ግብሩ አስቀድሞ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ዑማን ጨምሮ ታዋቂ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች በራስ መኮንን ድልድይ አካባቢ ችግኝ ተክለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም