‘‘የኔ ጉዞ ’’ የተሰኘ የአገር አቋራጭ አውቶቡስ ተጠቃሚዎች ቲኬት የሚያገኙበት አገልግሎት ይፋ ሆነ

538

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 12/2012 (ኢዜአ) በአገር አቋራጭ አውቶቡስ ተጠቃሚዎች ካሉበት ቦታ ሆነው ቲኬት የሚቆርጡበት የኦንላይን ክፍያ አገልግሎት ዛሬ ይፋ ተደረገ።

አገልግሎቱ ክፍያ ፋይናንሽያል ቴክኖሎጂ የተባለው ተቋም ከትራንስፖርት ሚኒስቴርና ከአገር አቋራጭ አውቶቡስ ማኅበራት በመተባበር መዘጋጀቱ ተገልጿል።

የክፍያ ፋይናንሽያል ቴክኖሎጂ የቢዝነስ ዴቪሎፕመንት ኃላፊ አቶ አቤኔዘር ወንደሰን በአገልግሎቱ ማስጀመሪያ መርሀግብር ላይ እንደገለጹት አግልግሎቱ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አለው።

አገልግሎቱ ከዚህ በፊት በተቋሙ ተቋርጦ የነበረውን የኢቲኬቲንግ አሰራር በማሻሻል በዘመናዊ መልኩ እንደሚጀምር አስረድተዋል።

የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ እንደተናገሩት አገልግሎቱ ተጓዦች ቲኬት ለመቁረጥ ወደ መናኽሪያ ለመሄድ ያጋጥማቸው የነበረውን እንግልትና ጊዜ ብክነት ይቀንሳል።

 ከዚህ በላይ የኮሮና ቫይረስ ሥርጭትን ለመከላከል ሚናው ከፍተኛ ነው ብለዋል።

 አገልግሎቱ በቀጣይ በከተሞች በባቡርና በሌሎች የሕዝብ ማመላለሻ ዘዴዎች እንደሚተገበር ሚኒስትሯ  ተናግረዋል።

ተቋሙ አገልግሎቱን ለጊዜው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ”ሲቢኢ ብር” በኩል የሚጀምር ሲሆን፣ በቀጣይ በ15 ባንኮች ለማስፋፋት መታቀዱን በመርሀግብሩ ላይ ተገልጿል።