በአዲስ አበባ ለ401 የከተማ ግብርና አርሶ አደሮች የግብአት ድጋፍ ተደረገ

94

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 12/2012 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ለ401 የከተማ ግብርና አርሶ አደሮች የማዳበሪያና የምርጥ ዘር ድጋፍ አደረገ።

የክፍለ ከተማው ዋና ሥራአስፈጻሚ አቶ ፍቃዱ ካሣሁንና የአዲስ አበባ የከተማ ግብርና ኮሚሽን ኮሚሽነር ወይዘሮ ፈትያ መሀመድ በክፍለ ከተማው ወረዳ አንድ ለቡ ኤርቱ ጀሞ አካባቢ በመገኘት ድጋፉን አስረክበዋል።

የከተማ አስተዳደሩ በከተማ ግብርና የተሰማሩ አርሶ አደሮችን ለማበረታታትና ምርትና ምርታማነትን ለማረጋገጥ  በትኩረት እየሰራ መሆኑን አቶ ፍቃዱ ገልጸዋል።

በተለይም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና ገበያው ወጥነት እንዲኖረው የከተማ ግብርና እጅግ አስፈላጊ ነው ብለዋል።

በዚህም ክፍለ ከተማው በወረዳ አንድ ለቡ ኤርቱ ጀሞ ለሚገኙና በከተማ ግብርና ለተሰማሩ 401 አርሶ አደሮች 750 ኩንታል ማዳበሪያ፣ 50 ኩንታል የጤፍና 150 ኩንታል የስንዴ ምርጥ ዘር በድጋፍ አበርክቷል።

በቀጣይም ለአርሶ አደሮቹ የሚያስፈልገውን ግብአት ለማሟላት በቅርበት እንደሚሰራም ጠቁመዋል።

አርሶ አደሩ መሬቱን በሕገወጥ መንገድ ከመሸጥና ከማከራየት ተቆጥቦ ምርትና ምርታማነት ማሳደግ ላይ ትኩረት በማድረግ ኢኮኖሚውንና ራሱን ሊያሳድግ እንደሚገባም አሳስበዋል።

በከተማዋ የሚታየውን የዋጋ ግሽበት ለማረጋጋትም የከተማ ግብርና ከፍተኛ ሚና አለው ብለዋል።

በዚህም በከተማ ግብርና የተሰማሩ አርሶ አደሮች ከራሳቸው አልፈው ለከተማዋ ነዋሪ በቂ የምርት አቅርቦት እንዲኖር ተሳትፏቸውን እንዲያጎለብቱ ጥሪ አቅርበዋል።

አርሶ አደሩ ከሕገወጥ ደላሎችና ንግድ ሊቆጠብ ይገባል ያሉት ዋና ሥራአስፈጻሚው ክፍለ ከተማው የገበያ ትሥሥር በመፍጠር ረገድ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራልም ብለዋል።

የአዲስ አበባ የከተማ ግብርና ኮሚሽን ኮሚሽነር ወይዘሮ ፈትያ መሀመድ እንዳሉት "በከተማዋ ያሉ አርሶ አደሮችና ከተማዋ ከዘርፉ ማግኘት ያለባቸውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ሳያገኙ በርካታ ጊዜያት አልፈዋል።"

በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት የምርት እጥረት እንዳይከሰትና ዜጎች ለችግር እንዳይጋለጡ በከተማ ግብርና የተሰማሩ አርሶ አደሮችን መደገፍ ያስፈልጋል ብለዋል።

የከተማ አስተዳደሩ ዘርፉን ለማሻሻልና በከተማ ግብርና የተሰማሩ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ለማድረግ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑንም አመልክተዋል።

ኮሚሽኑ የአርሶ አደሩን አቅም ለማሳደግና በቴክኖሎጂ የተደገፈ የአስተራረስ ዘዴን እንዲከተሉ ለማድረግ  የትራክተርና የውኃ መሳቢያ ፓምፖችን በድጋፍ ለማቅረብ ተዘጋጅቷል ብለዋል።

በከተማ ግብርና የተሻለ ውጤት ካላቸው አገራት ልምድ በመውሰድ የአርሶ አደሮቹን ግንዛቤ ማሳደግ ላይ ያተኮሩ በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውንም አንስተዋል።

በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ በከተማ ግብርና የተሰማሩ ከ7 ሺህ 600 በላይ አርሶ አደሮች ያሉ ሲሆን ከ750 በላይ ሔክታር መሬት መዘጋጀቱን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም