የኦሮሚያ ክልል በመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገለፀ

80

ጎባ፣  ሰኔ 12/2012 (ኢዜአ) የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የህብረተሰቡን ችግሮች ለማቃለል የጎላ ፋይዳ ባላቸው የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ላይ አተኩሮ እየሰራ መሆኑን በክልሉ በምክትል ፕሬዝዳንት ማዕረግ የገጠር ክላስተር አስተባባሪ ዶክተር ግርማ አመንቴ ገለጹ፡፡

በዶክተር ግርማ የተመራው የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በባሌ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች ግንባታቸው ተጠናቀው ለአገልግሎት የበቁ ፕሮጀክቶችን በማስመረቅ ወደ ስራ ለማስገባትና በግንባታ ሒደት ላይ ያሉትን ፕሮጀክቶች ለመመልከት ትናንት በባሌ ዞን ተገኝቷል።

በምክትል ፕሬዝዳንቱ ከተመረቁት የልማት ፕሮጀክቶች መካከል በባሌ ሮቤ ከተማ ከ10 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተሰራው ዘመናዊ የመዋእለ ህጻናት ትምህርት ቤት ይገኝበታል፡፡

ትምህርት ቤቱ በተቀመጠለት ጊዜና በጀት ከመጠናቀቁም ባሻገር የህጻናት መጫወቻና ማረፊያ፣መጻህፋት ቤትና ሌሎች የመማሪያ ክፍሎች ባካተተ መልኩ የተሰራ ነው ተብሏል።

ከተባበሩት አረብ ኢምሬቶች በተገኘው የገንዘብ ድጋፍ የተሰራው መዋእለ ህፃናት የሁለቱ ሀገራት የላቀ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ማሳያ እንደሆነም በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ ተገልጿል፡፡

ዶክተር ግርማ አመንቴ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት የክልሉ መንግስት የማህበረሰቡን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮችን በማቃለል ተጠቃሚነቱን ይበልጥ ለሚያረጋግጡ የልማት ፕሮጀክቶች ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው፡፡

በባሌ ዞን በተለያዩ ወረዳዎች ውስጥ ለአገልግሎት የበቁትና በመሰራት ላይ የሚገኙት የልማት ፕሮጀክቶች የዚሁ ጥረት አካል ናቸው ብለዋል፡፡

ዶክተር ግርማ በባሌ ሮቤ ከተማ እየተሰሩ የሚገኙ የንጹህ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክት  ፣በኮንክሪት እየተሰራ የሚገኘው ዘመናዊ የመኪና መናኽሪያ ፣ የውስጥ ለውስጥ አስፓልት መንገድ ፣የኢንዱስትሪ ፓርክና ሌሎች ፕሮጀክቶች በምን ያህል ፍጥነትና ጥራት እየተሰሩ መሆናቸውን በመጎብኘት በአፈፃፀማቸው ላይ ከተቋራጮችና ከአካባቢው ማህበረሰብ ተወካዮች ጋር ተመካክረዋል፡፡

የኦሮሚያ ኮንስትራክሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ዳንኤል መሳይ በበኩላቸው ዘንድሮ በክልሉ ውስጥ እየተሰሩ የሚገኙ የልማት ፕሮጀክቶች በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ፣ በጀትና በተሻለ የጥራት ደረጃ ተሰርተው ለአገልግሎት እንዲበቁ ክትትልና ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

በባሌ ሮቤ እየተገነቡ በሚገኙ የልማት ፕሮጀክቶች ዙሪያ መሻሻል ስለሚገባቸው ጉዳዮች ላይ ከተቋራጮችና ሌሎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውጤታማ ውይይት መደረጉን ጠቁመዋል።

በባሌ ሮቤ በፌዴራልና በክልሉ መንግስት፣ በተባበሩት አረብ ኢምሬቶች ድጋፍና መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ከ3 ቢሊዮን ብር በሚበልጥ በጀት 62 የልማት ፕሮጀክቶች በመከናወን ላይ እንደሚገኙ ከከተማ አስተዳደሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም