ግብፅ በህዳሴ ግድብ ላይ ያላት ተቃውሞ ፓለቲካዊ እንጂ ሳይንሳዊ ምክንያት የለውም... ግብፃዊው ምሁር

77

ሰኔ 12/2012 (ኢዜአ) ግብፅ በህዳሴ ግድብ ላይ የምታነሳው ተቃውሞ ፓለቲካዊ እንጂ ሳይንሳዊ ምክንያት የለውም ሲሉ የስነ ምድር ምሁር ፍሩዝ አልባዝ ተናገሩ።

ግድቡ የተገነባበት ቦታ ብዙ ጥናት የተደረገበት መሆኑንም ገልጸዋል።

ምሁሩ ከኤም ቢ ሲ አረብኛ ዩቲዩብ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደገለጹት “የግድቡ ውሃ ሙሌት ግብፅን ለውሃ ዕጥረት ይዳርጋል” ተብሎ የሚወራው የግብጽ ፖለቲከኞችና መገናኛ ብዙሃኗ ፕሮፓጋንዳ እንጂ እውነታን የተከተለ አይደለም።

ምሁሩ አክለውም ግድቡ የውሃው ፍሰት ላይ የሚያመጣው ይህ ነው የሚባል ተፅዕኖ የሌለው ነው ብለዋል።

በሌላ በኩል የህዳሴ ግድብ ግንባታ ደረጃውን የጠበቀ አይደለም ተብሎ የሚናፈሰው ወሬ ግድቡ ብዙ ጥናት ተደርጎበትና በዓለም አቀፍ ኩባንያ እየተገነባ በመሆኑ የደህንነት ስጋት ሊነሳበት አይገባም ብለዋል።

ግንባታውን የሚያከናውነው ኩባንያም ቢሆን ብር ተቀብለው ሊፈርስ የሚችል ነገር ሊገነቡ አይችሉም ያሉት ምሁሩ፤ “የአካባቢው መሬት ይንቀጠቀጣል ተብሎ የሚወራው ምንም እውቀት የሌላቸው የግብጻዊያን ወሬ ነው” ብለዋል።

ዲዛይኑም ሆነ ግንባታው በበቂ ጥናት ላይ የተመሰረተና ደረጃውን የጠበቀ በመሆኑ በግድቡ ለይ የጥራት ጥያቄ ለማንሳት የሚያስችል አንዳችም አመክንዮ አለመኖሩን ምሁሩ ተናግረዋል።

እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ ግብጽ ጉዳዩን ፖለቲካዊ ከማድረጓ ይልቅ ሳይንሳዊ ሁኔታው ላይ የተመሰረተ ድርድር ቢደረግ መልካም መሆኑን ጠቁመዋል።

ግብፅ ከአፍሪካ በቀዳሚነት ደረጃ ላይ የሚያስቀምጣት የከርሰ ምድር ውሃ ባለቤት እንደሆነችና ለምዕተ ዓመት የሚያገለግላት መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም