ተቋማቱ ለኮሮና መከላከያ ከ22 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የንፅህና መጠበቂያዎች ድጋፍ አደረጉ

70

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 11/2012 ( ኢዜአ) መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ለኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ቅድመ መከላከልና ምላሽ መስጠት የሚውሉ ከ22 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ ቁሳቁስና የንፅህና መጠበቂያዎች ድጋፍ አደረጉ።

ድጋፉን ያደረጉት ቶታል ኢትዮጵያ፣ የኢትዮጵያ መድሃኒት ፋብሪካ አክሲዮን ማህበር፣ የትራንስፖርት አሰሪዎች ፌዴሬሽን፣ የኢትዮጵያ ባሕረተኞች እና ቪዥን ፈንድ ማክሮ ፋይናንስ ናቸው።

ድጋፉን የተረከቡት ደግሞ የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስና በብሔራዊ ድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ የሃብት አሳባሳቢ ንዕስ ኮሚቴ ሰብሳቢ አምባሳደር ምስጋናው አርጋ ናቸው።

ሚኒስትሯ ድጋፉን ሲረከቡ በአገራችን ኮቪድ-19 እያደረሰ ያለውን የችግር ጫፍ ገና አላየንም ብለዋል።

እያጋጠመን ያለውን ችግር መወጣት የምንችለው ደግሞ ሁላችንም ባለን ነገር ድጋፍና ትብብር ስናደርግ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ለትራንስፖርት ዘርፉና ለሌሎች ተቋማት የተደረገው ድጋፍ የዘርፉን ተጋላጭነት ለመቀነስ ያግዛልም ብለዋል።

አሽከርካሪዎችና አጋሮቻቸው እንደ ጤና ባለሙያዎች ሁሉ ከፊት ሆነው ወገኖቻቸውን እያገዙ በመሆኑ ድጋፍ ሊደረግላቸው እንደሚገባም አመለክተዋል።

'ከፊታችን ያለው ፈተና ከባድ ነው' ያሉት ሚኒስትሯ ሁሉም የጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ሚኒስትሯ ጠይቀዋል።

አምባሳደር ምስጋናው በበኩላቸው ኮቪድ-19ን ለመከላከል ለተደረገው አገራዊ ጥሪ ሁሉም የበኩሉን እየተወጣ ነው ብለዋል።

በዛሬው ድጋፍ ቫይረሱ የሚያደርሰውን ችግር ለመከላከል ማኅበራዊ ሃላፊነታችውን ለተወጡ ተቋማትም ምስጋና አቅርበዋል።

ሁለተኛው ዙር የድጋፍ ማሰባሰብ የተጀመረ መሆኑንም አምባሳደር ምስጋናው ገልጸዋል።

ቶታል ኢትዮጵያና የኢትዮጵያ መድሃኒት ፋብሪካ አክሲዮን ማኅበር 20 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር፣ የትራንስፖርት አሰሪዎች ፌዴሬሽን 900 ሺህ ብር፣ የኢትዮጵያ ባሕረተኞች 1 ነጥብ 73 ሚሊዮን ብር፣ ቪዥን ፈንድ ማክሮ ፋይናንስ 500 ሺህ ብር የሚያወጡ ቁሳቁስና የንጽህና መጠበቂያዎች አበርክተዋል።

ከተበረከተው ቁሳቁስ መካከል ማቀዝቀዣዎች፣ አልጋና ፍራሽ፣ ጄኔሬተርና የሙቀት መለኪያ መሳሪያዎች ይገኙበታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም