በኮቪድ መከላከል የቻይና-አፍሪካ ትብብርና ወዳጅነት ተጠናክሯል - የቻይና ፕሬዚዳንት

172

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 11/2012 ( ኢዜአ) ኮቪድ-19ን ለመከላከል የቻይና- አፍሪካ ትብብር፣ ወዳጅነትና መተማመን መጠናከሩን የቻይናው ፕሬዚዳንት ሺ ጂፒንግ ገለጹ።

ፕሬዚዳንቱ ይህን የገለጹት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን በጋራ መከላከል በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ በማተኮር በቪዲዮ የተካሄደው የቻይና-አፍሪካ ልዩ የመሪዎች ጉባኤ ሲጠናቀቅ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን ጨምሮ የአፍሪካ መሪዎችና የዓለም አቀፍ ተቋማት ኃላፊዎች ከፕሬዚዳንት ሺ ጂፒንግ ጋር በቪዲዮ ጉባኤው ተካፍለዋል።

ፕሬዚዳንት ሺ ጂፒንግ የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል በቻይና- አፍሪካ መካከል የተከናወኑ ሥራዎችና በቀጣይ መጠናከር ባለባቸው ጉዳዮች ላይ አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

ወረርሽኙን ለመከላከል ቁርጠኛ መሆን፣ የልማት ትብብር፣ የቻይና- አፍሪካን ወዳጅነት ማጠናከርና ተያያዥ ጉዳዮችን አንስተዋል።

በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ህይወት በመቅጠፍ በዓለም ምጣኔ ሃብት ላይ እያሳደረ ያለውን ጫና በማየት ትብብር ወሳኝ መሆኑንም ተናግረዋል።

ወረርሽኙን ለመከላከል በቻይና- አፍሪካ መካከል ያለውን መተባበርና መተጋገዝ ጠቅሰው፣ በዚህ ወቅት የቻይና-አፍሪካ ትብብር፣ ወዳጅነትና መተማመን መጠናከሩን ገልጸዋል።

በቻይናና በአፍሪካ መንግሥታትና ሕዝብ መካከል ያለው የቆየና የጠነከረ ወዳጅነት በዓለም ነባራዊ ሁኔታ ሊንገዳገድ እንደማይችልም በንግግራቸው ጠቅሰዋል።

ኮቪድ-19 አሁንም በአብዛኛው የዓለም አገራት ላይ ጉዳት እያደረሰ በመሆኑ፣ ቻይናና አፍሪካ ምጣኔ ሃብት በማረጋጋትና የዜጎችን ህይወት በመጠበቅ ወረርሽኙን ለመዋጋት እየሰሩ ነው ብለዋል።

በመሆኑም የዜጎችን ደህንነት በማስቀደም፣ አስፈላጊውን ሃብት በማንቀሳቀስና ትብብርን በማጠናከር ወረርሽኙ ሊያስከትለው የሚችለውን ጉዳት መቀነስ አለብን ሲሉም ተደምጠዋል።

አፍሪካ ለኮሮና ቫይረስ መከላከል ለምትሰጠው ምላሽ የሕክምና ቁሳቁሶችን ጨምሮ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ቻይና ዝግጁ መሆኗንም አረጋግጠዋል።

በተጨማሪም የቻይና-አፍሪካ ወዳጅነት የሕክምና ተቋማት ግንባታን ለማፋጠን እንደምትሰራ ተናግረዋል።

እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለጻ ቻይና  የኮሮና ቫይረስ ክትባት ላይ እያደረገች ያለው ምርምር ሲጠናቀቅና ሥራ ላይ ሲውል አፍሪካዊያን የመጀመሪያ ተጠቃሚ ይሆናሉ።

በሌላ በኩል “የቤልት ኤንድ ሮድ” ትብብርን፣ ቻይና ለአፍሪካ የምታደርገውን የብድር ስረዛና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን በንግግራቸው ዳሰዋል።

ቻይና ለአፍሪካ አገራት በጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር 2020 ማብቂያ የሚመለስ ከወለድ ነፃ ብድርን እንደምትሰርዝ ፕሬዚዳንት ሺ ጂፒንግ ገልጸዋል።

ቻይና በኮሮና ወረርሽኝ በአስከፊ ሁኔታ ለተጎዱና ከፍተኛ የገንዘብ እጥረት ለገጠማቸው የአፍሪካ አገራት የብድር መክፈያ ጊዜ ማራዘምን ጨምሮ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጋር በመተባበር ድጋፍ ታደርጋለች ብለዋል።

አፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና ለማጠናከር፣ ዘላቂ የልማት ግብን ለማሳካትና ሌሎች ለምትከውናቸው የልማት ሥራዎች ቻይና ድጋፏን ትቀጥላለች ብለዋል ፕሬዚዳንት ሺ ጂፒንግ። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም