የእንቦጭ አረምን ለማስወገድ የተቀናጀና በእውቀት ላይ የተመሰረተ መፍትሄ እንደሚያስፈልግ ተገለጸ

68

ባህር ዳር፣ ሰኔ 11/2012 ( ኢዜአ) በጣና ሀይቅ ላይ የተከሰተውን የእንቦጭ አረምን በዘላቂነት ለማስወገድ የተቀናጀና በእውቀት ላይ የተመሰረተ መፍትሄ እንደሚያስፈልግ ተገለጸ።

"ጣና ትናንት፣ ዛሬ እና ነገ" በሚል መሪ ሃሳብ እምቦጭ መከላከልን መሰረት ያደረገ የፓናል ውይይት ዛሬ በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ተካሄዷል።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ፈንታ ማንደፍሮ በፓናል ውይይቱ ወቅት እንደገለጹት በሃይቁ ላይ የተከሰተውን የእንቦጭ አረም ለማስወገድ ባለፉት ስምንት ዓመታት በርካታ ጥረቶች ተደርገዋል።

በተለይም የባህር ዳር እና ጎንደር ዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁም በውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በጉልበትና ቴክኖሎጂዎችን በማቅረብ አግዘዋል።

የተደረገው ጥረት ያህል ለውጥ ማምጣት አለመቻሉን ጠቅሰው፤ ለዚህም የቅንጅት መጓደል መታየቱን አመልክተዋል።

ለሃይቁ ስጋት የሆነውን የእንቦጭ አረም ከሃይቁ በዘላቂነት ለማስወገድ በተናጠል ሳይሆን የተቀናጀና  በእውቀት ላይ የተመሰረተ መፍትሄ  እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

"በአሁኑ ወቅት ለክልሉ መንግስት ከጣና ሀይቅ የበለጠ ልዩ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ የለም "ያሉት ዶክተር ፈንታ ለዚህም የሚከፈለውን ዋጋ ሁሉ በመክፈል ሃይቁን ከስጋት ለማውጣት እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

እምቦጭን ከሃይቁ ለማንሳት በሚደረገው ጥረት ሁሉ የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑንም  አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ የክርሰ ምድር ውሃ መገኛው የጣና ሀይቅ በመሆኑ መላ ኢትዮጵያዊያን ሀይቁን ከጥፋት ለመታደግ በሚደረገው ርብርብ የድርሻቸውን እንዲወጡም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

"ጣና፣የውሃ መቀነስና የእንቦጭ መስፋፋት" በሚል የመነሻ ጽሁፍ ያቀረቡት የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ መምህር አቶ ምን ይችል ግታው ጣና ሀይቅ ለእምቦጭ አረም መስፋፋት በተለየ ሁኔታ ምቹና ተስማሚ ነው ነው ብለዋል።

ወደ ሃይቁ የሚገባው ከፍተኛ ደለል እምቦጭ በቀላሉ እንዲባዛ የሚያደርገው በመሆኑ የጋራ እቅድ በማውጣት በትብብር መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።

ለዚህ ደግሞ የክልሉ መንግስት ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር እንዳለበት ጠቁመው ፤በሰው ኃይልም ሆነ በቴክኖሎጂ አሁን ላይ ርብርብ ካልተደረገ የሀይቁ ህልውና አደጋ ላይ እንደሚወድቅ ገልጸዋል።

የአባይ ግድብን ለመገንባት እውቀቱን፣ ሃብት እና ጉልበቱን እያፈሰሰ ያለ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ጣናን መታደግ እስካልቻለ ድረስ በከንቱ ልፋት  እንዳይቀር  ሊያስቡበት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

"የክልሉ መንግስት ዩኒቨርሲቲዎች የሚያወጧቸውን ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂዎች በስራ ላይ እንዲውሉ በመፍቀድ በኩል ውስንነት አለበት "ያሉት ደግሞ የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ፍሬው ተገ ናቸው፡

የዩኒቨርሲቲው በሃይቁ ለመታደግ  "ሜካኒካል " እና "ባዮ ኬሚካል "ቴክኖሎጂዎችን ያቀረበ ቢሆንም በስራ ላይ እንዲውሉ በማድረግ በኩል ችግሮች ይስተዋላሉ ሲሉ ጠቅሰዋል።

ችግሩን በፍጥነት ማቃለል  የሚቻለው የዩኒቨርሲቲዎችን አቅም መጠቀም ሲቻል በመሆኑ የክልሉ መንግስት ከተቋማቱ ጋር  በቅርበት መስራት እንደሚጠበቅበት አመልክተዋል።

የጣና ሃይቅ በአሁኑ ወቅት ከሁለት ሺህ ሄክታር በላይ በእንቦጭ አረም እንደተወረረ በፓናል ውይይቱ ወቅት ተገልጿል።

በፓናል ውይይቱ የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ወርቀ ሰሙ ማሞ ፣ የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ መምህራንና ተመራማሪዎች እንዲሁም ባለ ድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም