የለውጥ እንቅስቃሴዎችን እንደሚደግፉ በወሎ ዩኒቨርሲቲ ተመራቂ ተማሪዎች ገለጹ

63
ደሴ ሐምሌ1/2010 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የጀመሯቸውን የለውጥ እንቅስቃሴዎችን እንደሚደግፉ በወሎ ዩኒቨርሲቲ ተመራቂ ተማሪዎች ገለጹ፡፡ በዩኒቨርሲቲው የደሴ ካምፓሱ በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች በመጀመሪያ፣ በሁለተኛና በሶስተኛ ዲግሪ ያሰለጠናቸው ሦስት ሺህ 334 ተማሪዎች አስመርቋል፡፡ ከተመራቂዎቹ መካከል በየጨቅላ ህጻናት ህክምና ትምህርት ክፍል 3 ነጥብ 98 በማምጣት የአጠቃላይ ዋንጫ ተሸላሚ የሆነው እንደሻው በላይሁን ዘመኑ ይገኝበታል፡፡ ተመራቂ እንዳሻው በሰጠው አስተያየት " ተማሪዎች ልዩነታችን አጥብበንና አንድነታችን አጠናክረን ለሀገርና ለህዝብ የሚጠቅም ስራ የሚሰሩበት ጊዜ አሁን ነው" ብሏል፡፡ ወጣቱ በጎ ተሞክሮዎችን በማስፋት የሀገሩን የቀደመ ገናናነት መመለስ እንዳለበት ጠቅሶ   በተሰማራበት ሙያ የህጸናት ሞት በመቀነስ ተተኪው ትውልድ ጤናማና አምራች እንዲሆን ለማድረግ መዘጋጀቱን ተናግሯል፡፡ በኮምቦልቻ ቴክኖሎጂ ኢንስቲቲዩት የኮምፒውተር ሳይንስ 3 ነጥብ 94 በማምጣት የዋንጫ ተሸላሚ የሆነችው መቅደስ አበራ በበኩሏ አሁን ለተመራቂ ተማሪዎች ብሩህ የአንድነት ጊዜ መሆኑን ገልጻለች፡፡ "በዘር የመለያየት፣ በኃይማኖት የመከፋፈልና በጠባብ አስተሳሰብ የመገፋፋት ባህላችን ተጠናቅቆ የመደመርና የመፈቃቀርን አዲስ ምዕራፍ የሚቀጥልበት ወቅት ነው" ብላለች። ትውልዱ ጥላቻን ከሚቀሰቅሱ መጠፋፋትን ከሚያስከትሉ ምክንያት አልባ ግጭቶች ተላቅቆ ለሀገሩ እድገት በተሰማራበት መስክ የበኩሉን ማበርከት እንዳለበትም አመለክታለች፡፡ መቅደስ የተማረችው የኮምፒውተር ሳይንስ እውቀት በመጠቀም የአገልግሎት አሰጣጡን የማዘመን፣  በጊዜና በጉልበት የሚደርሰውን ብክነት ለመቀነስ እንደምትሰራ ገልጻለች፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የጀመሯቸውን የለውጥ እንቅስቃሴዎች በመደገፍ ለሀገራዊ አንድነቱ እውን መሆን የበኩላቸውን እንደሚወጡ ተመራቂ ተማሪዎቹ ተናግረዋል፡፡ የወሎ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር አበተ ጌታሁን በዛሬው የምረቃ ስነስርዓት ወቅት እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው በማኅበረሰብ አገልግሎት፣ በስራ ፈጠራና ጥራቱን የጠበቀ የመማር ማስተማር እንዲኖር ባደረገው ጥረት የተሻለ ለውጥ እያስመዘገበ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በተለይ ጥራቱን የጠበቀ ስርዓት ትምህርት ለመዘርጋት የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ ዩኒቨርሲቲው ከተለያዩ ተቋማት የተውጣጡ 579 መምህራንን በሁለተኛና በሶስተኛ ዲግሪ መርሃ ግብር እያሰለጠነ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ከአንድ ሺህ በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች የስራ እድል መፍጠራቸውን አመልክተው በምርምር ዘርፉም በታዋቂዋ የባህል ዜማ ተጫዋች ማሪቱ ለገሰ የተሰየመውን ማሪቱ የተባለውን አዲስ የሽምብራ ዝርያ ከስድስት ዓመታት በኋላ ማስተዋወቁ ጠቁመዋል፡፡ ዶክተር አባተ ፈጠራው አርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት በማሳደግ በምግብ እህል ራስን ለመቻል የሚደረገውን ጥረት እንደሚያግዝ አስረድተዋል፡፡ ወሎ ዩኒቨርሲቲ የዛሬዎቹን ጨምሮ በአስር ዙሮች ከ30 ሺህ በላይ ተማሪዎችን አስመርቋል፡፡      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም