በኮሮና ዙርያ የተሰሩ ከ20 በላይ ጥናቶች በኦንላይን ኮንፈረንስ ለውይይት በመቅረብ ላይ ናቸው

390

መቐለ፣ ሰኔ 10/2012 (ኢዜአ) በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ዙሪያ ሙሁራን ያከናወኑዋቸው ከ20 በላይ ጥናቶች አራት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለሚሳተፉበት የኦንላይን የውይይት መድረክ በመቅረብ ላይ መሆናቸውን የመቐሌ ዩኒቨርሲቲ ገለጸ።

በመቐለ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሣይንስ ኮሌጅ የምርምርና የማኅበረሰብ አገልግሎት ኃላፊ ዶክተር አዲሱ ዓለማየሁ እንደተናገሩት በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ዙሪያ የተሰሩ ከ20 በላይ ጥናቶች አራት ከፍትኛ የትምህርት ተቋማት ከዛሬ ጀምሮ ለሁለት ቀናት በቪዲዮ ኮንፈረንሱ እየተወያየባቸው መሆኑን ተናግረዋል።

የኦንላይን ኮንፍረንሱ ምሁራን በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ዙሪያ ያከናወኑዋቸው ጥናቶች ለማሳወቅና ቫይረሱን አስመልክቶ የዕውቀት ሽግግር ለማድረግ ያለመ ነው ብለዋል።

ውይይቱ ላይ የመቐለ፣ አዲስ አበባ፣ ባሕርዳርና ሐረማያ ዩኒቨርሲቲዎች ምሁራን የተሳተፉበት መሆኑን ዶክተር አዲሱ ተናግረዋል።

ጥናታዊ ጽሑፎቹ ኅብረተሰቡ በኮሮና ቫይረስ ላይ ያለው ግንዛቤ፣ የሕክምና ባለሙያዎች ቫይረሱን ለመከላከል ያላቸው ዝግጅነትና የሚገጥሟቸው ችግሮች፣ ቫይረሱን ለመከላከል ባህላዊ መድኃኒቶች እንዴት መጠቀም እንደሚቻል የሚያመላክቱ ናቸው ብለዋል።

አብዛኛው ኅብረተሰብ በመገናኛ ብዙሃን በሚተላለፉ መልዕክቶች አማካኝነት ስለኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የተሻለ ግንዘቤ እንዲኖረው ማድረጉን በጥናቶቹ ተጠቅሷል።

ግንዛቤው ወደ ዕውቀት በመቀየርና በአተገባበር ላይ ያለው ችግር  ቀጣይ ሥራ እንደሚፈልግም በጥናቱ ተጠቁሟል።

ኮሮና ለመከላከልና በቫይረሱ የተያዙ የማኅበረሰብ ክፍሎች ለማከም በጤና ባለሙያዎች ያለው ዝግጁነት አጥጋቢ  ሆኖ አልተገኘም ተብሏል።

በመሆኑም የጤና ባለሙያዎች ራሳቸውን ከቫይረሱ ለመከላከልና የታመመውን ለማከም ያላቸውን የዝግጁነት ማነስ በቀጣይ መስከተካከል አለበት የሚል ምክረ ሀሳብ ቀርቧል።

በኦንላይን ኮንፈረንሱ ላይ ከተሳተፉት መካከል በባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ሕክምናና ጤና ሣይንስ ኮሌጅ መምህር ግዛቸው ታደሰ እንዳሉት ኮንፈረንሱ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ኮሮና ቫይረስ ለመከላከል እያደረጉት ያለው ጥናትና ምርምር የሚፈትሽ ሆኖ አግኝቸዋለሁ ብለዋል።

የኦንላይን ኮንፈረንሱ ከጠበቁት በላይ ነው ያሉት መምህር ግዛቸው እንዲህ ዓይነት ኮንፈረንስ በሁሉም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መቀጠል እንዳለበት ጠቁመዋል።

መምህር ግዛቸው አገሪቱ ኮሮና ቫይረስ ለመከላከል እየሄደችበት ያለው ሥርዓት ምን ይመስላል በሚል ዙሪያ ባቀረቡት ጥናት እንዳመለከቱት በለይቶ ማቆያ ማዕከላት የሚገኙ ወገኖች በስድስት ቀናት ውስጥ የጤንነታቸው ሁኔታ ማወቅ እንደሚቻል ዓለም አቀፍ ጥናቶች ዋቢ በመጥቀስ አብራርተዋል።

“የጤና ባለሙያዎች በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ላይ ያላቸው ዕውቀትና ቫይረሱን የሚከላከሉበት መንገድ” በሚል ርዕስ ጥናት ያቀረቡት ደግሞ በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ መምህር ጥላሁን አብዴታ ናቸው።

በሻምቦ ከተማ የሚገኝ ሻምቦ ጠቅላላ ሆስፒታል በተደረገው ጥናት መሠረት የጤና ባለሙያዎች በቫይረሱ ዙሪያ ያላቸው ግንዛቤና የመከላከል ዝግጁነት ዝቅተኛ እንደሆነ ማረጋገጣቸውን መምህር ጥላሁን በጥናታቸው ጠቅሰዋል።