በአዳማ ከተማ አካባቢን በማጽዳት፣ ደም በመለገስና ሰልፍ በማካሄድ ለጠቅላይ ሚኒሰትር ዶክተር አብይ አህመድ ድጋፍ ተደረገ

898

አዳማ ሐምሌ 1/2010 በአዳማ ከተማ ሕብረተሰቡና ወጣቶች አካባቢን በማጽዳት፣ ደም በመለገስና ሰልፍ በማካሄድ ለጠቅላይ ሚኒሰትር ዶክተር አብይ አህመድ ያላቸውን ድጋፍ አሳይተዋል።

ትናንት ማምሻውን የአዳማ ከተማ የመደመርና የፍቅር አስተባባሪ ኮሚቴ ድጋፉ ልማታዊ ስራዎችን በማከናወን ነው ቢልም ዛሬ የተወሰኑ ወጣቶች ሰልፍም አካሄደዋል።

 

የአስተባባሪ ኮሚቴው አባላት “ከዚህ በኋላ ከጠቅላይ ሚኒሰትሩ ጎን መሆን የሚቻለው የልማት ስራዎችን በማከናወን ነው” በማለት ከዋዜማ ጀምሮ ደም በመለገስና ታማሚዎችን በመጠየቅ አሳልፈዋል።

አባላቱ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጎን መሰለፋችንን የምናረጋግጠው የልማት ስራዎች ላይ ስንሳተፍ ብቻ ነው” ብለው አንጋፋውን የኦሮሚኛ የሙዚቃ ዘፋኝ አርቲስት ኑሆ ጎበናን በመጠየቅ የ50 ሺህ ብር ድጋፍም አድርገዋል።

ዛሬም ኢዜአ በስፍራው እንደታዘባው አስተባባሪ ኮሚቴውና የከተማዋ ወጣቶች በተወሰኑ የከተማዋ አካባቢዎች የጽዳት ስራዎችን ማከናወን ችለዋል።

የአስተባባሪ ኮሚቴው አባላትም ከሌሎች የከተማዋ ወጣቶች ጋር ከትናንት ጀምሮ ደም በመለገስና አካባቢን በማጽዳት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጎን መሆናቸውን አሳይተዋል።

ወጣቶቹ በቀጣይም ይህንኑ ተግባር አጠናከረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።

በከታማዋ በገዳ ከፍለ ከተማ የአካባቢ ጽዳት ሲያከናውኑ ያገኘናቸው ወይዘሮ እመቤትም “ጠቅላይ ሚኒስትሩን ማገዝ የሚቻለው የልማት ስራዎችን በማከናውን ነው” ብለዋል።

ይሁን እንጂ በርከት ያሉ ወጣቶች በከተማ አስተዳደሩ እውቅና ያላገኘ ሰለማዊ ሰልፍ በማካሄድ በከተማዋ አዳባባይ ያካሄዱ ሲሆን የተለያዩ ሰንደቅ ዓላማዎችንም አውለብልበዋል።

ሰልፈኞቹ የተለያዩ መፍክሮችንም በማሰማት በከተማዋ ዋና መንገዶች ላይ ሲዘዋወሩ ታይተዋል።