ዕድሮች እያደረጉት ያለው ድጋፍ አርአያ በመሆኑ ሊጠናከር ይገባል

87

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 10/2012(ኢዜአ) የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በአገሪቷ መከሰቱን ተከትሎ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለከተማ ወረዳ 6 አስተዳደር 400 ለሚሆኑ አነስተኛ ገቢ ላላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ዛሬ የምግብ ድጋፍ ተደርጓል።

የምግብ ድጋፉን ያደረገው በወረዳው የሚገኘው "ቀበሌ 43 አጠቃላይ ዕድር" ሲሆን በዚህም አነስተኛ ገቢ ላላቸው የዕድሩ አባላትና ሌሎች ድጋፍ የሚሹ ወገኖች 300 ሺህ ብር የሚገመት የምግብ ድጋፍ አድርጓል።  

የምግብ ድጋፍ ለማድረግ በተዘጋጀው መረሀግብር ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አለሙ አሰፋ በከተማዋ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ድጋፍ የሚፈልጉ የህብረተሰብ ክፍሎች መለየታቸውን ገልጸዋል።

"በመንግስት ከሚደረገው ድጋፍ በተጨማሪ የተለያዩ አካላትም የበኩላቸውን እገዛ ካላደረጉ ችግሩ የከፋ እንደሚሆን ጠቁመው ዕድሩ ያደረገው ድጋፍ ለሌሎች አርአያ በመሆኑ ሊጠናከር ይገባል" ብለዋል።

መንግስት የከፋ ጊዜ ቢመጣ በሚል በከተማዋ ከ1 ሺህ 200 በላይ የምግብ ባንኮች ቢያዘጋጅም የሁሉም አካል ርብርብ ካልታከለበት ውጤታማ እንደማይሆን ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ ከ7 ሺህ የሚበልጡ ዕድሮች መኖራቸውን የጠቆሙት አቶ ዓለሙ፣ ሁሉም "የበኩላቸውን ድጋፍ ካደረጉ ችግሩን ማቅለል ይቻላል" ብለዋል።

አነስተኛ ገቢ ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎችና በኮሮናቫይረስ ምክንያት ከቤት ወጥተው መስራት የማይችሉ ወገኖች ለርሃብ እንዳይጋለጡ የተጀመረው ድጋፍ መጠናከር እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለከተማ የወረዳ 6 ሥራአስፈጻሚ አቶ ጌታቸው አየለ በበኩላቸው ከ270 በላይ አነስተኛ የገቢ ምንጭ ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ተለይተው ድጋፍ እየተደረጉላቸው መሆኑን ገልጸዋል።

በተጨማሪም በወረዳው ያሉ ቤት አከራዮች ወረርሽኙ እስኪያልፍ ድረስ በቤት ኪራይ ላይ ቅናሽ እንዲያደርጉ ህብረተሰቡን በማወያየት ሰፊ እንቅስቃሴ መደረጉን ገልጸዋል።

በቀጣይም የአቅመ ደካማዎችን ቤት መጠገንን ጨምሮ በተለያየ መልክ ድጋፍ የማሰባሰቡ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል።

የቀበሌ 43 አጠቃላይ ዕድር የበላይ ጠባቂ አቶ ግርማ ፈለቀ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከሰትን ተከትሎ መንግስት አነስተኛ ገቢ ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች ለመርዳት ባስተላለፈው ጥሪ መሰረት ዕድሩ ድጋፍ ማድረጉን አስረድተዋል።

በዚህም የዕድሩ አባላት ሆነው አነስተኛ የገቢ ምንጭ ላላቸው የህብረተሰብ ክፍሎችና በወረዳው አነስተኛ ገቢ ላላቸው ሌሎች ወገኖች ከ300 ሺህ ብር በላይ በማውጣት የተለያየ ምግብ ድጋፍ መደረጉን ነው የገለጹት።

በቀጣይም ይህንን ተግባር አጠናቅረው እንደሚቀጥሉ አቶ ግርማ አስታውቀዋል።

የምግብ ድጋፍ ከተደረገላቸው መካከል ወይዘሮ በየነች ገብሬ በአነስተኛ የጡረታ ገቢ አራት የቤተሰ አባላትን እንደሚያስተዳድሩ ተናግረዋል።

በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ቤት መዋል በመጀመራቸው ለከፋ ችግር መጋለጣቸውንና በዕድሩ በኩል ለተደረገላቸው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

አቶ ታደሰ ቡታ የተባሉ ነዋሪ በበኩላቸው መተዳደሪያቸው አነስተኛ የጡረታ ገቢ መሆኑና ተንቀሳቅሰው መስራት አለመቻላቸው ከበሽታው በላይ ርሃብ ስጋት እንደሆናቸው ገልጸዋል።

ዛሬ በተደረገላቸ የምግብ ድጋፍ ደስተኛ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም