በደቡብ ወሎ ከ100 ሺህ ሔክታር መሬት በኩታ ገጠም የማልማት ስራ እየተካሔደ ነው

73

ደሴ፣ ሰኔ 10/2012 (ኢዜአ) በደቡብ ወሎ ዞን አርሶ አደሩ ራሱን ከኮረና ቫይረስ በመጠበቅ ከ100 ሺህ ሔክታር በላይ መሬት በኩታ ገጠም የእርሻ ዘዴ ለማልማት እየተሰራ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ፡፡

በመምሪያው የሰብል ልማት ቡድን መሪ አቶ ይመር ሰይድ እንደገለጹት በኮሮና ምክንያት የምግብ አቅርቦት እጥረት እንዳይፈጠር የሚያስችል የምርት ጭማሪ ለማስመዝገብ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው።

በዚህም ለመጪው የመኽር አዝመራ በዘር ለመሸፈን ከታቀደው 442 ሺህ ሄክታር መሬት ውስጥ ከ100 ሺህ ሄክታር በላይ የሚሆነውን በኩታ ገጠም የአመራረት ዘዴ ለማከናወን እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል ።

ከ180 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን በማሳተፍ በሚካሄደው የሰብል ልማት ለአካባቢው ስነ ምህዳርና የአየር ንብረት ተስማሚ የሆኑ የማሽላ፣ የማሾ፣ የቦለቄ፣ የቢራ ገብስ፣ የጤፍና የስንዴ ሰብሎች ለመዝራት እንቅስቃሴ ተጀምሯል ።

በኩታ ገጠም በዘር ለመሸፈን የታሰበው ማሳም እስከ ሦስት ጊዜ ደጋግሞ የታረሰ ከመሆኑም በላይ ከሶስት ሺህ ሄክታር በላይ የሚሆነው መሬት እስካሁን በዘር የተሸፈነ ሲሆን ቀሪውን ለማከናወን በቅንጅት እየተሰራ ይገኛል።

ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችል ሁለት መቶ ሺህ ኩንታል ማዳበሪያና 18 ሺህ ኩንታል የተለያዩ ምርጥ ዘሮች መሰራጨቱን  ጠቁመው ከአምስት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል ፡፡

እንደ አቶ ይመር ገለጻ አርሶ አደሩ በኩታ ገጠም ማልማቱ የተለያዩ ተባዮችን ለመከላከል፤ ግብዓት ለማቅረብ፤ ምርታማነትን ለማሳደግና ድጋፍና ክትትል ለማድረግ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል፡፡

በዞኑ አልፎ አልፎ ብቅ ጥልቅ የሚለውንና ከፍተኛ ስጋት የፈጠረውን የአንበጣ መንጋ ለመከላከልም አርሶ አደሩ በንቃት ማሳውን እንዲያስስና መረጃ እንዲሰጥ እስከ ቀበሌ ድረስ መዋቅር ተዘርግቶ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

በጃማ ወረዳ የ015 ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ሙህዬ ተስፋው በበኩላቸው ከአንድ ሄክታር የሚበልጥ መሬት ስንዴና ጤፍ በኩታ ገጠም ለማልማት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል፡፡

የተለያዩ ግብዓቶችንም ተጠቅመው ከ30 ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ከኮሮና ቫይረስ ራሳችን እንድንጠብቅ የግብርና ባለሙያዎች ልዩ ድጋፍ እያደረጉልን ነው ያሉት አርሶ አደሩ በኩታ ገጠም ማልማታችን ግብዓት በወቅቱ እንድናገኝና ተባይን በጋራ እንድንከላከል እድል ፈጥሮልናል ብለዋል፡፡

ሌላው የወግዴ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ሰይድ መሃመድ በበኩላቸው ሁለት ሄክታር የሚጠጋ መሬት ጤፍ በኩታ ገጠም ለማልማት ማሳቸውን እንዳለሰለሱ ገልጸዋል፡፡

አካባቢው ለጤፍ ምቹ በመሆኑ የተለያዩ ግብዓቶችን ተጠቅሜ ከ45 ኩንታል በላይ ምርት እጠብቃለሁ ያሉት አርሶ አደሩ  ባለፈው ዓመትም ከዚሁ ማሳ ላይ 41 ኩንታል አግኝቻለሁ ብለዋል፡፡

ምንም እንኳ እስከ ዛሬ በደቦና በጋራ ስራዎችን ብንሰራም ዘንድሮ በኮረና ቫይረስ ስጋት ምክንያት የየራሳችንን እያለማን እንገኛለን የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።

በደቡብ ወሎ ዞን አጠቃላይ በመኸር ከሚለማው 442 ሺህ ሄክታር መሬት ከ12 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም