ዲላ ዩኒቨርሲቲ በ5 ሚሊዮን ብር ወጪ ያስገነባው የሥነ ሕዝብና የጤና ምርምር ማዕከል ተመረቀ

116

ዲላ፣ ሰኔ 10/2012 (ኢዜአ) ዲላ ዩኒቨርሲቲ በአምስት ሚሊዮን ብር ወጪ በወናጎ ወረዳ ያስገነባው የሥነ ሕዝብና የጤና ምርምር ማዕከል ዛሬ ተመርቆ ለአገልግሎት ዝግጁ መሆኑን ገለጸ።

የዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ችሮታው አየለ በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ እንደተናገሩት ማዕከሉ በጌዴኦ ዞን ወናጎ ወረዳ የተገነባ ሲሆን በዋናነት በአከባቢው የሚስተዋለውን ከፍተኛ የሆነ የሕዝብ መጠጋጋት የሚያስከትለውን ችግር በምርምርና ጥናት ለመቅረፍ ይሰራል።

እንዲሁም በሥነ ተዋልዶ ዙሪያና በሌሎች የጤና ጉዳዮች ምርምር በማካሄድና በማስተማር ኅብረተሰቡን ለማገዝ ጥረት እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ማዕከሉ ለወጣቶች የውይይት ዕድል የሚፈጥርና ዕውቀት የሚገበዩበት ይሆናል ነው ያሉት።

በቀጣይ የሰው ኃይልና ግብዓቶችን በማሟላት፣ የምርምር ሥራ ለሚሰማሩ ምሁራን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

የጌዴኦ ዞን አስተዳደሪ አቶ ገዙ አሰፋ በበኩላቸው በወናጎ ወረዳ በአንድ ስኩየር ኪሎ ሜትር ውስጥ ከ1 ሺህ 200 በላይ ሕዝብ የሚኖርበትና ከፍተኛ ጥግግት እንዳለ ገልጸዋል።

በሥነ ተዋልዶ ጤና ዙሪያ ግንዛቤ ለመፍጠርም ሆነ በጥግግቱ ሳቢያ የሚመጡ ችግሮችን በምርምር ለመለየት የማዕከሉ መገንባት አስተዋጽኦው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል። 

ማዕከሉ የሕዝብ እንደመሆኑ መጠን ወደ ፊት ዩኒቨርሲቲው ለሚሰራው የምርምር ሥራ ኅብረተሰቡ ተገቢውን መረጃ በመስጠት ትብብር እንዲያደርግ አሳስበዋል።

ማዕከሉ በጤናና በሥነ ተዋልዶ የምርምር መረጃዎች ምንጭ እንዲሁም የምርምር ውጤቶችን በአካባቢ ለሚገኘው ኅብረተሰብና ለጤና ተቋማት ለማድረስ የሚረዳ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ጤናና ሕክምና ሣይንስ ኮሌጅ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ሰላማዊት አየለ ናቸው።

በሥነ ተዋልዶ መስክ የመጀመሪያና የሁለተኛ ዲግሪ የምርምር ሥራ የሚከናወንበት በመሆኑ ጠቀሜታው ከዩኒቨርሲቲውና ከማኅበረሰቡ አልፎ ለሀገር የጎላ ፋይዳ እንዳለው አብራርተዋል።

ከምረቃው ሥነ ሥርዓት ጎን ለጎን የዩኒቨርሲቲውና የጌዴኦ ዞን ከፍተኛ አመራሮች የችግኝ ተከላ መረሃ ግብር አካሔደዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም