ሪፍት ቫሊ ዩኒቨርሲቲ 7 ሺህ 775 ተማሪዎችን አስመረቀ

163
ነቀምቴ ሐምሌ 1/2010 ሪፍት ቫሊ ዩኒቨርሲቲ ነቀምቴ ካምፓስ በተለያዩ የሙያ መስኮች ያሰለጠናቸውን 7 ሺህ 775 ተማሪዎች አስመረቀ፡፡ በዛሬው ዕለት ለምረቃ ከበቁት መካከል 7 ሺህ 104 የሚሆኑት በመጀመሪያ ዲግሪ የተመረቁ ሲሆን 671 በቴክንክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና መርሀ ግብር ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የቆዩ ናቸው። ከአጠቃላይ ተመራቂዎች መካከልም 3ሺህ 892 የሚሆኑት ሴቶች መሆናቸው ተመልክቷል። የካምፓሱ ዲን አቶ ወንድሙ ቀኖ እንዳሉት ተመራቂ ተማሪዎቹ በዩኒቨርሲቲው በመደበኛ፣ በማታ፣ በክረምት፣ በዕረፍት ቀናትና በተልዕኮ የትምህርት መርሀ ግብሮች ትምህርታቸውን የተከታተሉ ናቸው፡፡ ሪፍት ቫሊ ዩኒቨርሲቲ  ነቀምቴ ካምፓስ በነቀምቴ ከተማ የመማር ማስተማር ሥራውን ከጀመረበት 2000 ዓ.ም ጀምሮ የዛሬ ተመራቂዎች ጨምሮ 25ሺህ 440 ተማሪዎችን በተለያዩ ሙያዎች አሰልጥኖ አስመርቋል። ዩኒቨርሲቲው ከ5ኛ ክፍል ጀምሮ እስከ 10ኛ ክፍል በተልዕኮ ተማሪዎችን ተቀብሎ በማስተማር ላይ መሆኑንም ጨምረው አመልክተዋል፡፡ በተቋሙ ያገኙት ዕውቀት ለተሰማሩበት የመንግስትና የግል ሥራ አጋዥ እንደሆናቸው ለምረቃ የበቁ አንዳንድ የዕለቱ ተመራቂዎች ተናግረዋል፡፡ ከተመራቂዎቹ መካከል የወለጋ ዩኒቨርሲቲ ሠራተኛ አቶ አመንቴ ወዬሳ በሰጡት አስተያየት ካላቸው የሕግ ዲፕሎማ ላይ በዩኒቨርሲቲው በቢዝነስ ማናጅመንት መመረቃቸው ሕብረተሰቡን በተሻለ ለማገልገል እንደሚረዳቸው ተናግረዋል፡፡ የሦስት ልጆች እናት የሆኑት ወይዘሮ እስከዳር ጳውሎስ በበኩላቸው የመንግሥት ሥራ እየሰሩ በማታ ክፍለ ጊዜ በአካውንትንግ በመጀመሪያ ዲግሪ መመረቃቸውን ገልጸው፣ በተማሩት ትምህርት በተቋሟቸው ውስጥ ውጤታማ ሥራ ለመስራት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል። በዕለቱ በትምህርታቸው ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎች የተዘጋጀላቸውን የዋንጫና የሜዳሌያ ሽልማት ከዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ዲሪብሳ ዱፌራ እጅ ተቀብለዋል ሲል የዘገበው ኤዜአ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም