የቱሪዝም ዘርፉ እንዲያገግም የሚያደርግ አዲስ ስትራቴጂ ይፋ ሆነ - ኢዜአ አማርኛ
የቱሪዝም ዘርፉ እንዲያገግም የሚያደርግ አዲስ ስትራቴጂ ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ ሰኔ 9/2012(ኢዜአ) በኮቪድ-19 ምክንያት የተጎዳው የቱሪዝም ዘርፍ መልሶ እንዲያገግምና ወደ አዲስ ምዕራፍ እንዲሻገር ያስችላል የተባለ አዲስ ስትራቴጂ በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ይፋ ሆነ።
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከተከሰተ ማግስት ጀምሮ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ላይ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ማሽቆልቆልና ግሽበት አስከትሏል።
በተለይ በዓለም ቱሪዝም ዘርፍ ያሳረፈው ጫና ቀላል የማይባል ሲሆን በኢትዮጵያም ባለፉት 3 ወራት በመስኩ ከፍተኛ መቀዛቀዝ ታይቷል።
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በወረርሽኙ ሳቢያ የተፈጠረውን ጫና ለመቋቋምና ዘርፉ መልሶ እንዲያገግም ብሎም ወደተሻለ ምዕራፍ እንዲሻገር የሚያስችል ስትራቴጂ ይፋ አድርጓል።
በስትራቴጂው እንደ ሆቴል ያሉ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በተቀመጠው ዓለም አቀፍ መስፈርት መሰረት ለተገልጋዮች በቂ የኮሮና ቅድመ መከላከል አገልግሎት እንዲሰጡ ይደረጋል።
በዘርፉ ሰንሰለት ውስጥ የሚገኙ እንደ ትራንስፖርት፣ አስጎብኚ ድርጅቶችና ሌሎች ተሳታፊዎችም ይህንኑ ተግባራዊ እንዲያደርጉና የተገልጋዩን ደህንነት እየጠበቁ እንዲሰሩም ያስችላል።
ለጎብኚዎች አመቺ እንዲሆን ዓለምአቀፍ ፕሮቶኮል አሟልቶ መገኘት፣ በቴክኖሎጂ የታገዘ የጥቅል አገልግሎት/ፓኬጅ/ ማዘጋጀት፣ ግልጽ፣ ወጥ እና ተከታታይ መረጃ በአንድ ማዕከል መስጠት ይገኙበታል።
ከክልሎች ጋር ያለው ትስስር ይበልጥ የሚጠናከርበት ይሆናል በተባለው ስትራቴጂ መዳረሻ ስፍራዎችን የማዘመን ስራም እንደሚሰራ ተጠቁሟል።
ጎብኚዎች በተንቀሳቃሽ የእጅ ስልካቸው ተጠቅመው በቀላሉ ክፍያ የሚፈጽሙበት አሰራርና የጥሪ ማዕከል ለተገልጋዮች መዘርጋትም ይገኙበታል።
በተጨማሪም ከጎረቤት አገራት ጋር ትስስር በመፍጠር በተለይ የምስራቅ አፍሪካ አገራትን የቱሪስት መስህብነት በጋራ የመሸጥ ስራዎችም በስትራቴጂው የሚሰሩ ይሆናል ነው የተባለው።
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ካሳው እንደገለጹትም የኮሮናቫይረስ በአገሪቷ መከሰቱ ከታወቀ በኋላ እንዴት መቋቋምና መሻገር ይቻላል በሚሉ ተግባራት ላይ በስፋት መሰራቱን አንስተዋል።
ስትራቴጂው በኢትዮጵያ የቱሪዝም መስክ እየተሰራ የነበረውን ስራ መልሶ የማገገም ተግባር ለመስራት ብቻ ሳይሆን አዲስ ከፍታን ይዞ ይመጣል ተብሎ የሚጠበቅ ነው ብለዋል።
ስትራቴጂው ሲዘጋጅ የውጭ ምሁራን ጭምር ተሳትፈውበትና ሰፊ ዝግጅት ሲደረግበት ቆይቶ መፅደቁን ነው ሚኒስትሯ የገለጹት።
በባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የዓለም አቀፍ ቱሪዝም ፋሲሊቴሽን ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ደርበው በበኩላቸው ስትራቴጂው የተፈጠረውን ችግር እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ዘርፉ ከጉዳት ወጥቶ እንዲፈነጠር ለማድረግ የሚያስችል ነው ብለዋል።
የአዲስ አበባ ሆቴል ባለቤቶች ማኅበር ሰብሳቢ አቶ ቢኒያም ብስራት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሲነሳና ሆቴሎች ወደ ስራ ሲመለሱ የኮሮናን ቫይረስ የመከላከል ብቃት ላይ ሆነው መገኘት አለባቸው ብለዋል።
በስትራቴጂው መሰረት የዘርፉ አካላት ኮሮናን በብቃት እየተከላከሉ ስራዎችን መከወን ከቻሉ በቱሪዝም ዘርፍ አዳዲስ ስኬቶችን ማስመዝግብ ይቻላል ነው ያሉት።
በስትራቴጂው ከሚተገበሩ ተግባራት መካከል የአገር ውስጥ ቱሪዝምን ማሻሻል ሌላው የትኩረት አቅጣጫ ሲሆን በዘርፉ አዳዲስ ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነም ተገልጿል።