ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ለአምባሳደሮች የስራ መመሪያ ሰጡ

80

አዲስ አበባ ሰኔ 9/2012(ኢዜአ) ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ኢትዮጵያን በተለያዩ የዓለም አገራት ለሚወክሉ አምባሳደሮች የሹመት ደብዳቤና የስራ መመሪያ ሰጡ።

ፕሬዚዳንቷ በተለያዩ አገራት ኢትዮጵያን እንዲወክሉ ለተሾሙ አምባሳደሮች የስራ መመሪያ በመስጠት አሸኛኘት አድርገውላቸዋል።

አዲሶቹ ተሿሚ አምባሳደሮች በሚሄዱበት አገር የኢትዮጵያን መልካም ግንኙነትና ወዳጅነት በማጎልበት ወደ ተሻለ ደረጃ እንዲያደርሱም አሳስበዋል።

አምባሳደሮች የወከሉትን መንግስትና ሕዝብ ግንኙነት በማጠናከር በኩልም በቆይታቸው ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም እንዲሁ።

ኢትዮጵያ በምጣኔ ሃብትና በተለያዩ ዘርፎች ለያዘቻቸው ዕቅዶች ግብዓት የሚሆኑ ጠቃሚ አሰራሮችን በማየት እንዲሰሩም መክረዋል።

ወቅቱ ዓለም በኮሮና ወረርሽኝ ፈተና ውስጥ የገባችበት በመሆኑ የሚነደፉ አዳዲስ መፍትሄዎችን ለኢትዮጵያ በሚሆን መልኩ እንዲያጠኑም ጠቁመዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው በበኩላቸው ኢትዮጵያ በሁለትዮሽና በባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲ መስኮች ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስከበር እየሰራች እንደምትገኝ ገልጸዋል።

በዚህም የፖለቲካ፣ የምጣኔ ሃብት፣ የቴክኒክና አቅም ግንባታ ድጋፎች እንዲሁም ለተጀመሩ ፕሮጀክቶች የልማት ፋይናንስና የተራዘመ ብድር በማስገኘት ውጤታማ የዲፕሎማሲ ስራዎችን እየሰራች ነው ብለዋል።

አዲስ ተሿሚ አምባሳደሮች ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ለአገራቸው ሁለንተናዊ እንቅስቃሴና ብሔራዊ ጥቅም የማስከበር ስራዎች ድጋፍ እንደሚደረግ አረጋግጠዋል።

ሽኝት የተደረገላቸው አምባሳደሮችም የተጣለባቸውን ሃላፊነት ለመወጣት ያላቸውን ዝግጁነት ገልጸዋል።

በብራስልስ ቤልጂየም ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሂሩት ዘመነ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት የሁለቱን አገራት ግንኙነት ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

በለንደን የእንግሊዝ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ተፈሪ መለስ በበኩላቸው በቴክኖሎጂ መስክ ሁለቱ አገራት በጋራ የሚሰሩበትን ሁኔታ ለማሳደግ እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

አሸኛኘት የተደረገላቸው አምባሳደሮች የችግኝ ተከላ መርሃ ግብርም አካሂደዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም