የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ለይፋዊ ጉብኝት ኤርትራ ገቡ

67
አዲስ አበባ ሀምሌ 1/2010 የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ለይፋዊ ጉብኝት ኤርትራ ገብተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤትና የህዝብ ተወካይ ምክር ቤት አፈጉባዔዎችንና የአፋር ክልል ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችን አስከትለው አስመራ ሲገቡ  የኤርትራዉ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ፣ የኤርትራ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ የኃይማኖት አባቶችና ከተለያየ ህብረተሰብ የተውጣጡ  ታዋቂ ኤርትራውያን ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል። የአስመራ ከተማ በኢትዮጵያ እና ኤርትራ ሰንደቅ ዓላማ የደመቀች ሲሆን፥ ወዳጅነትን የሚያጠናክሩ የተለያዩ መልዕክቶችም ተሰቅለውባታል፤ የሁለቱ ሀገሮች ብሄራዊ መዝሙሮችም ተዘምረዋል። በቅርቡ የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የሁለቱን አገራት ግንኙነት ለማደስ የአልጀርሱ ስምምነት ሙሉ በሙሉ እንዲተገበር ውሳኔ ማሳለፉን ተከትሎ  ኤርትራም የኢትዮጵያን የሰላም ጥሪ በመቀበል በቅርቡ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ የሚመራ ልዑክ ወደ አዲስ አበባ መላኳ አይዘነጋም። የኤርትራ የልዑካን ቡድን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ ጋር ካደረጉት ውይይት በተጨማሪ የሀዋሳን ኢንዱስትሪ ፓርክ  ጨምሮ የተለያዩ ጉብኝቶችን  ማድረጉ ይታወሳል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም