የኮሮና መመርመሪያ ላቦራቶሪዎች ዓለም አቀፍ የጥራት መለያ እንዲያገኙ እየተሠራ ነው

542

አዲስ አበባ ሰኔ 7/2020 የኮሮናቫይረስ መመርመሪያ ላቦራቶሪዎች የዓለም አቀፍ ደረጃዎች ድርጅት የጥራት መለያ እንዲያገኙ እየሠራ መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ አክሪዲቴሽን ጽሕፈት ቤት ገለጸ። 

ሁለት የኮሮናቫይረስ መመርመሪያ ላቦራቶሪዎችም የአክሪዲቴሽን አገልግሎት ጥያቄ አቅርበዋል። 

ጽሕፈት ቤቱ የአገሪቷ ምርትና አገልግሎቶች ዘላቂ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት እንዲያገኙ ከማድረግ ባሻገር የኅብረተሰቡ ጤንነት እንዲጠበቅ ለሜዲካል ላቦራቶሪዎች ዓለም አቀፍ ማረጋገጫና እውቅና ይሰጣል።

የኮሮናቫይረስ የላቦራቶሪ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ቁጥር በየጊዜው እየተጨመረ ሲሆን ከ30 በላይ የሚሆኑ በመደበኛነት አገልግሎቱን በመስጠት ላይ ይገኛሉ።

በመሆኑም ጽህፈት ቤቱ ኮሮናቫይረስን ጨምሮ የሜዲካል ላቦራቶሪዎችን ጥራትና ደረጃ ማስጠበቂያ ዓለም አቀፍ የደረጃዎች ድርጅት መለያ እውቅና ለመስጠት እንቅስቃሴ ጀምሯል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ አክሪዲቴሽን ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ አርዓያ ፍስሀ ለኢዜአ እንደገለጹት ላቦራቶሪዎቹ ዓለም አቀፍ ሰርተፊኬት ‘አክሪዲቴሽን’ ማግኘታቸው ኮቪድ-19ን ለማጥፋት ሚና አለው።

አቶ አርዓያ ከወራት በፊት በኢትዮጵያ ኮቪድ-19 ላይ የሚሰሩ ላቦራቶሪዎች አገልግሎት በብዛት ባልተጀመረበት ወቅት ስለ አክሪዲቴሽን ማንሳት ተገቢ እንዳልነበረ አውስተዋል።

ሆኖም አሁን የአክሪዲቴሽን አገልግሎቱን ለመጀመር መነሻ የሆነው በመላ አገሪቷ የላቦራቶሪዎቹ ቁጥር መጨመርና ለተመሳሳይ ላቦራቶሪዎች ዓለም አቀፍ የአክሪዲቴሽን አገልግሎት መጀመር ነው ብለዋል።

ላቦራቶሪዎቹ የኮቪድ-19 ምርመራ ሲጀምሩ ጽህፈት ቤቱ ለንዑሳን መስፈርቶች አክሪዴት ማድረጉንና አሁን ዓለም አቀፍ ዕውቅና ለመስጠት አሰራሮች መዘርጋታቸውን አስታውቀዋል።

ሁለት ላቦራቶሪዎች የአክሪዲቴሽን ሰርተፊኬት ጥያቄ ለጽሕፈት ቤቱ ማቀረባቸውንም አክለዋል።

እንደ አቶ አርዓያ ገለጻ ከጽህፈት ቤቱ የአክሪዲቴሽን ተጠቃሚ ዘርፎች ከፍተኛውን ቁጥር የያዘውና ብዙ መስፈርቶች /ፓራሜትሮች/ በማስመዘገብ ቀዳሚው የሜዲካል ላቦራቶሪ ዘርፍ ነው።

ጽህፈት ቤቱ በ74 መስፈርቶች ለ53 የሜዲካል ድርጅቶች ዓለም አቀፍ የአክሪዲቴሽን እውቅና ሰጥቷል።

ይህም ከአገሪቷ የጥራት ፍላጎት አንፃር አነስተኛና ተመጣጣኝ አለመሆኑን ነው ያስረዱት።

ጽህፈት ቤቱ ከዓለም አቀፍ ደረጃዎች ድርጅት ካገኘው የአክሬዲቴሽን ዓለም አቀፍ ዕውቅና ከሜዲካል ላቦራቶሪዎች በተጨማሪ የፍተሻ፣ የምርትና የአገልግሎት ዘርፎችም ይገኙበታል።