በኦሮሚያ ክልል በክረምቱ በተለያዩ ትምህርት ቤቶች 30 ሺህ ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎች ይገነባሉ

163

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 6/2012 (ኢዜአ) በኦሮሚያ ክልል በዘንድሮው ክረምት ወራት በ10 ሺህ ትምህርት ቤቶች ውስጥ 30 ሺህ ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎችና ከ500 በላይ ቤተ መጽሐፍት በበጎ ፈቃደኞች እንደሚሰሩ ተገለጸ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ፣ የኦሮሚያ፣ የአማራና የሱማሌ ክልል ፕሬዚዳንቶች በተገኙበት ሁለተኛውን ዙር የኦሮሚያ ክልል የዜግነት አገልግሎት በዛሬው ዕለት በይፋ አስጀምረዋል።

በክልሉ ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ወሊሶ ከተማ ተገኝተው መርሃ ግብሩን ያስጀመሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ”በወሊሶ በመገኘቴ ትልቅ ደስታ ተሰምቶኛል” ብለዋል።

ወሊሶ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ትልቅ አሻራ ያኖሩ የእነ ባልቻ አባ ነፍሶ፣ ገረሡ ዱኪና የሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴ የትውልድ አካባቢ መሆኑንም አስታውሰዋል።

በመሆኑም በዚህ ሥፍራ ተገኝቶ ለኢትዮጵያ ዕድገትና ለዜጎች ሕይወት ለውጥ እጅግ ጠቃሚ የሆነውን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ማስጀመር ትልቅ ትርጉም አለው ብለዋል።

የበጎ ፈቃድ ሥራ የአደጉ አገራት ገናናነታቸውን ያረጋገጡበት አንዱ መንገድ መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለኢትዮጵያም ያስፈልጋታል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያን ለመገንባት ብቸኛው መንገድ ሥራና ልፋት በመሆኑ በተለይ የወጣቶች ነፃ አገልግሎት የማይተካ ሚና አለው ብለዋል።

”በበጎ ፍቃድ የሚከናወን ሥራ ኢንቨስትመንት ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ”መቼና እንዴት እንደሆነ መናገር ባይቻልም የሚከፍልበት ጊዜ አለ” ብለዋል።

ይህንኑ መርህ መሠረት በማድረግ በተለይም የክልሉ ወጣቶች አሁን ያለውን ነፃነት ተጠቅመው ለልማትና ለአንድነት የሚጠቅሙ ተግባራትን ማከናወን ይኖርባቸዋል ብለዋል።

ወጣቶች ”ታሪክ የምትሰሩበት ጊዜ አሁን ነው፤ ረጅም ርቀት የሚወስደን መንገድም ይኸኛው መሆኑን ማወቅና መተግበርም ተገቢ ነው” ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሕዝቡ ራሱን ከኮሮናቫይረስ በመጠበቅ በተጀመረው በጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ እንዲሳተፍም ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ፤ የበጎ ፈቃድ ወይም የዜግነት አገልግሎቱ መከባበር፣ መወዳደር፣ ተግቶ መሥራት፣ የጠራ ዕይታና ትብብርን ማዕከል አድርጎ ይከናወናል ብለዋል።

በአንደኛው ዙር የዜግነት መርሃ ግብር በክልሉ 12 ቢሊዮን ብር የሚገመት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተደርጓልም ብለዋል።

በዚህኛው ዙርም በክልሉ በሚገኙ 10 ሺህ ትምህርት ቤቶች በእያንዳንዳቸው ተጨማሪ ሦስት ክፍሎችን በድምሩ 30 ሺህ የመማሪያ ክፍሎች ይገነባሉ ብለዋል።

በተጨማሪም ከ500 በላይ ላይብረሪዎች፣ የአካባቢ ጥበቃ ሥራ፣ የአቅመ ደካሞች ቤት እድሳት የሚከናወኑ ሲሆን በዚህም ሰባት ሚሊዮን ሰዎች ይሳተፋሉ ብለዋል።

በበጎ ፈቃደኞች እንዲታደስ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ ያስጀመሩት በከፋ ችግር ውስጥ ኑሮን ተጋፍጠው ላሉት የወይዘሮ ፋጡማ ጋሊ ቤትን ነው።

”የሚደረገው እድሳት ትርጉም ያለውና ሕይወቴን ለማሻሻል ትልቅ ጥቅም ያለው በመሆኑ እጅግ ተደስቻለሁ” ብለዋል ወይዘሮ ፋጡማ።

በበጎ ፈቃደኝነት ሲሳተፍ የነበረው ወጣት ዘሪሁን ተስፋዬ በዚህ በተባረከ ተግባር ላይ መሳተፍ ትልቅ ዕረፍት ያስገኛል በማለት፤ በተለይ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሥፍራው ተገኝተው ይህን ሥራ በማስጀመራቸው መደሰቱን ተናግሯል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የበጎ ፈቃድ ሥራውን ባስጀመሩበት በወሊሶ ሊበን አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ ሦስት ክፍሎችን የሚሰሩ ሲሆን ወንበሮች፣ ኮምፒተሮችና መጽሐፍቶችንም አበርክተዋል።