የመዲናዋ ወጣቶች ኮቪድ- 19ን ከመከላከል በተጓዳኝ በጎ ተግባራትን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ተጠየቀ

96

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 6/2012 (ኢዜአ) የመዲናዋ ወጣቶች ኮቪድ -19ን ከመከላከል በተጓዳኝ በጎ ተግባራትን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የብልፅግና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋዬ በልጂጌ ጥሪ አቀረቡ።

ኃላፊው በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የክረምት በጎ ፈቃደኞች መርሀ ግብርን በይፋ አስጀምረዋል።

ኃላፊው መርሃ ግብሩን ባስጀመሩበት ወቅት እንደተናገሩት የከተማዋ ወጣቶች የኮሮና ቫይረስን በመከላከል እስካሁን የሚደነቅ ሥራ አከናውነዋል።

ወጣቶች በቀጣይነትም በክረምት የተለያዩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች ላይ የነቃ ተሳትፎ በማድረግ ውጤታማ ተግባራትን እንዲያከናውኑ ጠይቀዋል።

በተለይ የአሁኑን አስቸጋሪ ጊዜ በመተባበር፣ በመረዳዳትና በመተጋገዝ ልናልፈው ይገባል ብለዋል አቶ ተስፋዬ።

የዚህ ዓመት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሚከናወነው በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተውን የኮሮናቫይረስን እየተከላከልን በመሆኑ ተጨማሪ ጥረትን ይጠይቃል ብለዋል።

በዘንድሮው ክረምት የበጎ ፈቃድ መርሃ ግብር ኮቪድ 19ን መከላከል፣ የተቸገሩትን መደገፍ፣ የአቅመ ደካሞችን ቤት ማደስ፣ ችግኝ ተከላን ጨምሮ ሌሎችም መርሃ ግብሮች ይከናወናሉ።

የኮሮናቫይረስን በመከላከል ሂደት በጤና ባለሙያዎችና በመንግሥት የሚተላለፉ መመሪያዎችን በመተግበር መሆን እንዳለበትም አቶ ተስፋዬ አሳስበዋል።

አቶ ተስፋዬ መርሀ ግብሩን ካስጀመሩ በኋላ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ እየተከናወኑ ያሉ የከተማ ግብርና ሥራዎችን ጎብኝተዋል።

የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ይታያል ደጀኔ በበኩላቸው በክረምቱ የተለያዩ በጎ ተግባራትን ለማከናወን ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጸዋል።

በዚህ ዓመት ክረምቱን ጨምሮ በክፍለ ከተማው ብቻ የ700 አቅመ ደካማ ዜጎችን ቤት ለማደስ ዕቅድ መያዙንም ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ በክረምት በጎ ፈቃድ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ወጣቶች በተለያዩ የአገልግሎት ተግባራት ላይ መሰማራታቸው ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም