በኢትዮጵያ 280 ሴቶችና ህፃናት ጥቃት ተፈፅሞባቸዋል

154

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 06/2012 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ሦስት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ 280 ሴቶችና ህፃናት ጥቃት እንደተፈጸመባቸው አንድ ጥናት አመለከተ።

የሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚደርሰውን ጥቃት መከላከልና ጥቃቱ ሲፈጸም ምን አይነት ምላሽ መስጠት ይገባል በሚሉ ጉዳዮች ላይ በሴቶች ጉዳይ ከሚሰሩ ሲቪክ ማህበራትና ፌዴሬሽኖች ጋር ዛሬ እየተወያየ ነው።

በውይይቱ ላይ ከመጋቢት 1 ቀን 2012 እስከ ግንቦት 20 ቀን 2012 ዓ.ም ባሉት ጊዜያት በሴቶችና ህፃናት ላይ የደረሰውን ጥቃት የሚያብራራ ጥናት ቀርቧል።

ጥናቱ የሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር፣ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግና የአዲስ አበባ ሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ በጋራ ያስጠኑት ጥናት ነው።

በጥናቱ መሰረት በኢትዮጵያ በሁለት ወር ከሃያ ቀን ብቻ 280 ሴቶችና ህፃናት ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል፤ ከነዚህ ውስጥ 273ቱ ሴቶች ሲሆኑ ሰባቱ ወንዶች ናቸው ተብሏል።

ጥቃት ከደረሰባቸው ሴቶችና ህፃናት መካከል 215ቱ በአዲስ አበባ በሚገኙ አስሩ ክፍለ ከተሞች ነዋሪ ሲሆኑ ቀሪዎቹ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የሚኖሩ መሆናቸውን ጥናቱ አመላክቷል።

በሴቶችና ህፃናት ላይ የተፈጸሙት ጥቃቶች አስገድዶ መድፈር፣ ግብረሰዶምና ያለዕድሜ ጋብቻ መሆናቸውም በጥናቱ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም