በሰሜን ሸዋ ዞን ለሚገነባው ከ108 ኪሎ ሜትር በላይ የአስፓልት መንገድ የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠ

139

ደብረ ብርሃን፤ ሰኔ 6/2012 ( ኢዜአ) በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ከደብረ ብርሃን ጅሁር ደነባ ድረስ ለሚገነባው ከ108 ኪሎ ሜትር በላይ የኮንክሪት አስፓልት መንገድ ዛሬ የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠ።

የመሰረተ ድንጋዩን ያስቀመጡ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ናቸው።

ከደብረ ብርሃን በለሚ መገንጠያ አድርጎ ጅሁር ደነባ የሚደርሰው የአስፓልት መንገዱ ከሶስት ቢሊዮን 600 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደሚኖረው በዚሁ ወቅት ተገልጿል።
የመንገዱን ግንባታ የሚከናወነው ሰንሻይን በተበለ ሀገር በቀል ተቋራጭ ድርጅት ሲሆን በአራት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ ለአገልግሎት እንደሚበቃ ተገልጿል።

በተያዘለት የጊዜ ገደብ በማጠናቀቅ የአካባቢውን ምርት ወደ ገበያ በቀላሉ ለማውጣት፣ የገጠርና ከተማን ህዝብ ትስስር ለማቀላጠፍና ሌሎችንም ማህበራዊ ችግሮች ለመፍታት እንደሚያግዝ ተመልክቷል።

በተያያዘ ዜና በዞኑ ሞረትና ጅሩ ወረዳ ሰባት ሚሊዮን ብር በሆነ ወጪ የተገነባ የቁም እንስሳት ግብይት ማዕከልም ምክትል ጠቅላይ ሚነስትሩ በተገኙበት ተመርቋል።

የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ አቶ ተሾመ ተገኝ በምረቃው ስነሰርዓት ወቅት እንዳሉት የግብይት ማዕከሉ የተገነባው በግብርና እድገት ትራንስፎርሜሽን ትግበራ ፕሮግራም ነው።

ማዕከሉ አስፈላጊ መሰረተ ልማቶች የተሟሉለት በመሆኑ በእንስሳት ማድለብ ለሚታወቁት የአካባቢው አርሶ አደሮች ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል።
በስነ ስርዓቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፣ የትራንስፖርት ሚንስትር ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ፣ የብልጽግና ጽህፈት ቤት ኃላፊው አቶ ብናልፍ አንዷለም እና ሌሎችም የፌዴራል ፣ የክልልና የዞን አመራሮች ተገኝተዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሰዓት በኋላ በሰሜን ሸዋ ዞን ከሚገኙ የማህበረስብ ክፍሎች ጋር ውይይት እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም