ካስተዋልን እናልፈዋለን

132

አብዱራህማን ናስር(ኢዜአ)

የኮሮና ቫይረስ በአገራችን መገኘቱ ከተነገረ ሶስት ወራት ተቆጥረዋል። በመጋቢት ወር የመጀመሪያ ሳምንት በአንድ ጃፓናዊ ላይ የታየው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በየጊዜው እየሰፋና ቁጥሩም እየጨመረ በአሁኑ ወቅት ከ2900 በላይ ሲደርስ 47 ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል። በየእለቱ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ባለፉት ሁለት ወራት ከ10 በታች ከነበረበት አሁን ላይ በአንድ ቀን ወደ 200 የሚጠጋ ሰው በቫይረሱ እየተያዘ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል። በአሁኑ ወቅት የቫይረሱ ስርጭት አዲስ አበባን ማእከል አድርጎ በመላ አገራችን እየተስፋፋ ይገኛል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች የውጭ ሃገር የጉዞ ታሪክም ሆነ ከህሙማን ጋር የታወቀ ንክኪ የሌላቸው ሰዎች መገኘታቸው እንዲሁም በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ከቀን ወደቀን እየጨመረ መምጣቱ የኮሮናቫይረስ ወደ ማህበረሰቡ ውስጥ መግባቱን የሚያመለክት ነው። ከዚህ በተጨማሪ የኮሮናቫይረስ ምልክት የማይታይባቸው ህሙማን መገኘታቸው እንዲሁም ከሞቱ በኋላ በምርመራ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች መኖራቸው ስርጭቱን አሳሳቢ እንደሚያደርገው የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ። ባለሙያዎቹ እንደሚገልጹት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ማህበረሰቡ ውስጥ ከገባ በቀላሉ ከአንድ ሰው ወደ ተለያዩ ሰዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ የመዛመት እድል ይኖረዋል። ከሰሞኑ በአዲስ አበባ የተፈጠረው ሁኔታ ይህንኑ የሚያሳይ ነው።

የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ መረጃ እንደሚያመለክተው የቫይረሱ ስርጭት በከተማዋ በአስሩም ክፍለከተሞች የተስፋፋ ሲሆን እስካሁን ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር  እስከ ሰኔ 4/2012 ዓ.ም ድረስ 1946 ደርሷል፡፡ ይህም በአገሪቱ እስካሁን ከተመዘገበው 2900 ሰዎች ከ 70 በመቶ በላይ  ይሸፍናል። ቢሮው ሰኔ 04 ቀን 2012 ዓ.ም  ባወጣው መረጃ መሰረት በ24 ሰዓታት ውስጥ በተደረገ የላብራቶሪ ምርመራ 87 ሰዎች ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል። ከእነዚህም ውስጥ 2 የውጭ አገር የጉዞ ታሪክ ያላቸውና 4 ሰዎች በቫይረሱ ከተያዘ ሰው ጋር የታወቀ ግንኙነት ያላቸው መሆኑን መረጃው ያመለክታል። ይህ ሁኔታ የሚያመለክተው እያንዳንዳችን በየትኛውም ቦታና ጊዜ በቫይረሱ የመያዝ እድላችን በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ነው። እስካሁን በአገር አቀፍ ደረጃ የላቦራቶሪ ምርመራ የተደረገላቸው ሰዎች ቁጥር ወደ 170,860  ቢሆንም ተጨማሪ ምርመራ ቢደረግ በበሽታው የተያዘ ሰው ቁጥር አሁን ከተመዘገበው በእጅጉ ሊበልጥ እንደሚችል መገመት አያዳግትም።

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከላከልና መቆጣጠር የሚኒስትሮች ኮሚቴ መረጃ እንደሚጠቁመው በግንቦት ወር የመጀመሪያዎቹ 15 ቀናት የኮሮና ቫይረስ ስርጭት በ310 በመቶ ጨምሯል። በዚሁ መረጃ መሰረት በመጋቢት እና ሚያዝያ ወራት  53 ሺህ 600 ሰዎች ተመርምረው 286 ሰዎች ቫይረሱ የተገኘባቸው ሲሆን በግንቦት ወር የመጀመሪያ ሁለት ሳምንታት በተደረገው የ55 ሺህ 845 ሰዎች ምርመራ 886 ሰዎች ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል። ይህም አስራ አምስት ቀን ባልሞላው ጊዜ ውስጥ የቫይረሱ ስርጭት በሶስት እጥፍ ማደጉን ያመለክታል።

የቫይረሱ ስርጭት በዚሁ ፍጥነት ከቀጠለ በአጭር ጊዜ ለመቆጣጠር ወደ ሚያዳግትበት ደረጃ ሊሻገር ይችላል። ይህም እንደ አገርም ሆነ በግለሰብ ደረጃ የሚያስከትለው ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ስነልቦናዊ ጉዳት ከባድ ነው። ወረርሽኙ የሚያስከትለው አደጋ እጅግ የከፋ መሆኑን እንደ አሜሪካ፣ ጣሊያንና ስፔን ከመሳሰሉት የበለጸጉ አገራት መረዳት ይቻላል።  የኢኮኖሚ ባለሙያዎች እንደሚገልጹት ቫይረሱ በኢኮኖሚ በዳበሩ አገራት ማለትም በአውሮፓ እና አሜሪካ እንደተስፋፋው በአገራችን ቢዛመት ኢኮኖሚያችን የሚሸከምበት አቅም ስለማይኖረው የሚያደርሰው ተጽእኖ ከፍተኛ ነው።

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በአገራችን መከሰቱ ከተነገረበት እለት ጀምሮ የከፋ ጉዳት እንዳያስከትል መወሰድ ስለሚገባቸው የመፍትሔ እርምጃዎች በስፋት ሲሰራ ቆይቷል፡፡ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት አካላዊ ንክኪ እንዳይኖር ወይም ርቀትን መጠበቅ፣ እጅን በሳሙናና በውሃ በተደጋጋሚ መታጠብ፣ አፍንና አፍንጫን መሸፈን፣ አስገዳጅ ሁኔታ ካልገጠመ በስተቀር ከቤት አለመውጣት የሚሉትን መርሆዎች መሰረት በማድረግ ሕብረተሰቡ ግንዛቤ እንዲያገኝ ማደረግን ጨምሮ እንዲተገበር አስገዳጅ መመሪያዎችን በማውጣት ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል፤ እየተደረገም ይገኛል። በህብረተሰቡ ዘንድ ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ መዘናጋቱና ቸልተኝነቱ እየጨመረ መጥቷል።  

የጤና ሚኒስቴር ግንቦት 30 ቀን 2012 ባወጣው መግለጫ በ7 ቀናት ውስጥ ብቻ 848 ሰዎች በቫይረሱ እንደተያዙ እንዲሁም 16 ሰዎች ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተገናኘ ህይወታቸው ማለፉን አረጋግጧል። ይሁንና በህብረተሰቡ ዘንድ በሽታውን ለመከላከል የሚረዱ የመከላከያ ዘዴዎችን ከመተግበር አኳያ እጅግ ብዙ ክፍተቶች እየተስተዋሉ መሆኑን በመጥቀስ የበሽታው ስርጭት ተስፋፍቶ ከአቅም በላይ ከመድረሱና ለከፋ ችግር ከመዳረጋችን በፊት የጉዳዩን አሳሳቢነት በመረዳት ከምንጊዜውም በላይ አስፈላጊው የመከላከል ስራ እንዲተገበሩ በአጽንኦት አሳስቧል።

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ያልፋል፤ ሕይወት በነፃነት ትቀጥላለች፤ ነገር ግን እስከሚያልፍ ከቤተሰብ ጀምሮ በሁሉም ደረጃ የሚያስከትለው ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ስነልቦናዊ ጉዳት ከፍተኛ ነው። በዚህ ወቅት የምንወስዳቸው የጥንቃቄ እርምጃዎች ለራሳችን፣ ለቤተሰባችንና ለአገር የሚኖረው ፋይዳ ትልቅ ነው። ይህን ወቅት በማስተዋል፣ ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ መከላከል ከቻልን በእርግጥም እናልፈዋለን። ይህን ክፉ ጊዜ ለማለፍ ግን ቸልተኝነትን በመተው ሁሉም የሚጠበቅበትን በመወጣት ሊከሰት የሚችለውን ጉዳት ሊንከላከል ይገባል መልእክታችን ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም