ሀገሪቱ በሳይንስና ቴክኖሎጅ ዘርፍ ያለባትን ክፍተት ለመሙላት ተመራቂዎች የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል--የሳይንስና ቴክኖሎጅ ሚኒስትር

82
አዳማ ሰኔ 30/2010 ሀገሪቱ  በሳይንስና ቴክኖሎጅ ዘርፍ ያለባትን  ክፍተት ለመሙላት በሚደረገው ጥረት ተመራቂዎች የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ  የሳይንስና ቴክኖሎጅ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጅነር ጌታሁን  መኩሪያ ገለጹ። የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጅ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች በመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪ ያሰለጠናቸውን ከ1ሺህ 800 በላይ ተማሪዎችን ዛሬ አስመረቀ። ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጅነር ጌታሁን  መኩሪያ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት  ሀገሪቱ በተያያዘችው ፈጣን የልማትና የዕድገት ጎዳና እንድትቀጥል የኢንዱስትሪ፣ ማኑፋክቸሪንግና ኮንስትራክሽን መስኮችን በቴክኖሎጅ መደገፍና ማጋዝ ይገባል፡፡ ሀገሪቱ  በሳይንስና ቴክኖሎጅ ዘርፍ ያለባትን  ክፍተት ለመሙላት በሚደረገው ጥረት ውስጥ  ተመራቂዎች የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባም አስረድተዋል። የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጅ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንት ዶክተር ለሚ ጉታ በበኩላቸው የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጅ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች በመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪ አሰልጥኖ ካስመረቃቸው ተማሪዎች መካከል 21 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች መሆናቸውንም ገልጸዋል። ኘሬዝዳንቱ አያይዘውም ዩኒቨርሲቲው በ2030 ዓ.ም ከአፍሪካ ግንባር ቀደም የሳይንስና ቴክኖሎጅ የልህቀት ማዕከል ለመሆን ግብ አስቀምጦ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ለዚህም በኤሌክትሮኒክስ፣ በመስኖና የውሃ ሀብት ምንዲስና፣ ትራንስፖርቴሽን፣ የስፔስ ሳይንስን ጨምሮ ስምንት የልህቀት ማእከላት በማደራጀት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጠዋል። በሀገሪቱ ከሚገኙ  እፆዋት መድኋኒቶችን መቀመምና ማምራት የሚያስችል የሙያ ዘርፍ መመረቁን የገለጸው ደግሞ ተመራቂ ዲንቃ ሙሉጌታ ነው። በሴንቴስስ  ኦርጋኒክ ኬሚስትሪ ከተማሩት ሌሎች ሙያተኞች ጋር በመቀናጀት ሙያቸውን ማዕከል ያደረገ ሥራ ለመፍጠር መዘጋጀቱንም ገልጿል፡፡ ሌላው በጅኦማቲክስ ኢንጅነሪንግ  የተመረቀው  ሃጫሉ ቀዲዳ በበኩሉ በተማረው ሙያ ሀገሩንና ህዝቡን ለማገልገል ዝግጁ መሆኑን ገልጿል፡፡ ''አሁን በመንግስት የሚሰጠውን ሥራ አንጠብቅም'' ያለው ሃጫሉ በሙያው ከተመረቁት ጎደኞቹ ጋር በመደራጀት የራሳቸውን ሥራ ለመፍጠር መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም