ለአረንጓዴ አሻራ- ዘብ እንቁም

203

ወንድማገኝ ሲሳይ (ኢዜአ)

የአረንጓዴ ልማት የመጨረሻው አላማ ዘላቂ ልማትን ማስፈን ነው። የተባበሩት መንግስታት የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም እንደሚለው አረንጓዴ ኢኮኖሚ የዜጎችን የኑሮ ሁኔታ የሚያሻሽል፣ ማህበራዊ ፍትህን የሚያመጣ፣ የአካባቢ አደጋዎችንና ስነ-ምህዳራዊ እጥረቶችን በእጅጉ የሚቀንስ የልማት መንገድ ነው።

በሕገ-መንግስቱ አንቀጽ 44(1) መሰረት ሁሉም ሰዎች ንጹህና ጤናማ በሆነ አካባቢ የመኖር መብት እንዳላቸው ሲደነግግ በአንቀጽ 92(1) መሰረት ደግሞ መንግስት ሁሉም ኢትዮጵያዊ ንጹህና ጤናማ አካባቢ እንዲኖረው የመጣር ኃላፊነት አለበት።

በአንቀጽ 92(4) መሰረትም መንግስትና ዜጎች አካባቢያቸውን የመንከባከብ ግዴታ አለባቸው። ለዚህም ነው መንግስት ተፈጥሮንና ስነ-ምህዳርን በመጠበቅ የኢኮኖሚ እድገት ማምጣት እንደሚቻል በማመን ለተግባራዊነቱ እየሰራ የሚገኘው።

በዚህ ረገድ አንዱና ዋነኛው በሀገር አቀፍ ደረጃ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተነደፈው የአረንጓዴ አሻራ ቀን ተጠቃሽ ነው።

በመጀመሪያው ዙር «የአረንጓዴ አሻራ» ሃገር አቀፍ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር  በገጠርም ሆነ በከተማ ሁሉም ዜጋ በነቂስ ወጥቶ መሳተፉ ይታወሳል።

በተለይ በአንድ ቀን ብቻ ከ200 ሚሊዮን  ችግኝ በላይ በመትከል የዓለምን ሪከርድ መስበር መቻሉም እንዲሁ።

የዘንድሮው 2ኛ ዙር አገር አቀፍ የአረንጓዴ አሻራ ቀን ደግሞ በሀዋሳ ከተማ በይፋ ተጀምሯል።

በሐዋሳው ታቦር ተራራ ላይ ችግኝ የመትከል መርሃ ግብሩን በይፋ ያስጀመሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ናቸው።

በስነ ስርዓቱ ላይ ሚኒስትሮች፣ታዋቂ ግለሰቦች ፣ አትሌቶችና አርቲስቶች፣የሲዳማ ብሄረሰብ አባቶች፣የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና ካቢኔያቸው ተካፋይ ነበሩ።

በዚህ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትሩ  እንዳሉት በሀገሪቱ የደን ልማትን ለማስፋፋት ሁሉም ዜጋ በአንድ ልብና መንፈስ ሊነሳሳ ይገባል።

አምና በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከተተከሉት 4 ቢሊዮን ችግኞች ውስጥ እስከ አሁን ባለው ጥናት መሠረት 84 በመቶ  መፅደቃቸውን ገልጸው ይህ የሚያሳየው ልፋታችን ፍሬ ማሳየቱን ነው ይላሉ።

ደን ልማቱ ካስገኛቸው ትሩፋቶች ውስጥም ዘንድሮ ዓመቱን ሙሉ ማለት በሚያስችል መልኩ ዝናብ ሳይቆራረጥ መዝነብ መቻሉንም ለአብነት አንስተዋል።

ዘንድሮም ልማቱን ለማስቀጠል 5 ቢሊዮን ችግኞች ለማዘጋጀት የፌዴራልና የክልል መንግስታትና ባለድርሻ አካላት ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸውን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህ ዝግጅት ውጤታማ እንዲሆንና ፍሬ እንዲያፈራ የሁሉንም ተሳትፎ ይጠይቃል ብለዋል።

እያንዳንዱ ቤተሰብ በተቀመጠው እቅድ መሰረት በጓሮው ፣ በሰፈሩና በተመረጡ ቦታዎች ችግኝ በመትከል ክረምቱን እንዲያሳልፍ  ጥሪ አቅርበዋል ።

በዚህ ጉዳይ ላይ በእምነት ፣ በፆታና በፖለቲካ አመለካከት መለያየት የለብንም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የእምነት አባቶች ተከታዮቻቸውን በማሳመን ችግኝ እንዲተክሉ ነው የጠየቁት።

የፖለቲካ ሰዎች ደግሞ የፖለቲካ አመለካከታቸውን ለጊዜው ወደ ጎን በመተው አባላቶቻቸውን በማሳተፍ ጥረት እንዲያደርጉ መልእክት አስተላልፈዋል ።

ተማሪዎች፣መምህራን፣ወጣቶችና፣ሴቶችም በዚሁ አረንጓዴ አሻራ ላይ በመረባረብ ከተፈጥሮ ጋር በመተሳሰር ክረምቱን በመልካም ስራ እንዲያሳልፉ አደራ ብለዋል።

የደን ልማቱ ለራስ፣ለትውልድና ለሃገር የሚሰራ ስራ መሆኑን ሁሉም በመገንዘብ ለአላማው መሳካት በጋራ እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል።   

አሻራቸውን ሲያኖሩ ያገኘናቸው የፌዴራል የአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽነር ፕሮፌሰር ፍቃዱ በየነ እንዳሉት ከምንጠጣው ውሃ እስከ ምንተነፍሰው አየር፣ከምንመገበው ምግብ እስከ እራሳችንን ለማከም የምንጠቀምባቸው የመድሃኒት ዕፅዋቶች ሁሉ የብዝሀ ሕይወት ውጤቶች ናቸው።

በልዩ ልዩ ምክንያቶች ጉዳት ደርሶበት የነበረውን መሬት ወደ ነበረበት ለመመለስ በተከናወኑ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች በሺህ የሚቆጠር ሄክታር መሬት ስነ ህይወታዊ ሀብት ጭምር እንዲያገግም ማድረግ መቻሉን ይናገራሉ።

አዳዲስ ለሚገነቡ የማምረቻና ሰፋፊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት የአካባቢና የማህበራዊ ጉዳዮች አያያዝ ሥርዓት አበጅተናል ያሉት ፕሮፌሰሩ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሁለትዮሽና የባለ ብዙ መድረኮች ከልማት ፖሊሲዎች ጋር የሚጣጣሙ የቴክኒክና የመዋዕለ ንዋይ ድጋፍ ለማግኘት የሚያስችሉ ምቹ መደላድሎች ተፈጥረዋል።

ነገር ግን ዛሬም እንደ ሀገር ያልፈታናቸውና እያጋጠሙን ያሉ በርካታ የአካባቢ ችግሮች አሉብን ይላሉ።

በተለይ አነስተኛ ከሚባለው የኢንዱስትሪና አገልግሎት ዘርፍ የሚለቀቁ ተረፈ ምርቶች የአካባቢ ስነ ውበት ከማበላሸት በላይ ለብዝሃ ህይወት ሀብታችን ቀጣይነት ሌላ ስጋት መሆናቸውን አስረድተዋል።

ይህን ችግር ለማቃለል የአካባቢ ጥበቃ ስራዎች ወሳኝና መሰረታዊ በመሆናቸው የዘንድሮውን ሀገር አቀፍ የችግኝ ተከላ ፕሮግራም ላይ ሁሉም ዜጋና ባለድርሻ አካላት በመሳተፍ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

በመንግስት በኩል ከወረርሽኙ መከላከል በተጓዳኝ የዘንድሮውን ችግኝ ተከላ ለማስፈጸም ብሄራዊ ኮሚቴ ተቋቁሞ እስከታችኛው መዋቅር ድረስ ተናብቦ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

 አክለውም በችግኝ ተከላው ወቅት ከሚደረጉ ጥንቃቄዎች መካከል አንዱ ከአንዱ እንዳይገናኝ የመስመር ገደብ ተቀምጧል።

የቦታ ርቀትን ከመጠበቅ ባሻገር ጠዋትና ማታ በፈረቃ የችግኝ ተከላውን በማካሄድ የተያዘውን እቅድ ለማሳካት ጥረት እንደሚደረግ አብራርተዋል።

የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው በበኩላቸው አምና እንደ ሃገር በተመዘገበው የችግኝ ተከላ ሪከርድ የክልሉ ህዝብ በአንድ ጀምበር ከ52 ሚሊዮን በላይ ችግኝ በመትከል አሻራውን አሳርፏል።

የተከለውንም ችግኝ በመንክባከብ ኃላፊነቱን ሲወጣ ቆይቷል ያሉት አቶ ርስቱ ለዚህ ለተቀደሰ ተግባሩም ምስጋናቸውን ችረውታል።

ዘንድሮም ያጋጠመንን የኮሮና ቫይረስ ከመከላከል በተጓዳኝ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተቀመጠውን አረንጓዴ አሻራ እውን እንዲሆን የክልሉ ድርሻ የሆነውን 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል ዝግጅት መጠናቀቁን አስታውቀዋል።

በሐዋሳው ታቦር ተራራ ላይ በተካሔደው የአረንጓዴ አሻራ ቀን ማብሰሪያ ስነስርዓት ላይ ከተሳተፉ ታዋቂ ግለሰቦች መካከል ዝነኛዋ አትሌት ደራርቱ ቱሉ አንዷ ናት።

አትሌቷ በወቅቱ በሰጠችው አስተያየት ድርቅንና የአየር ንብረት ለውጥን ለመግታት በሚደረገው የአረንጓዴ ልማት እንቅስቃሴ ላይ ለሁለተኛ ጊዜ  በመሳተፏ ደስተኛ ናት ።