ምክር ቤቱ 6ኛውን ብሔራዊ ምርጫ ለማራዘም የቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ በአብላጫ ድምጽ አጸደቀ

351

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 3/2012 (ኢዜአ) የፌዴሬሽን ምክር ቤት ስድስተኛውን ብሔራዊ ምርጫ ለማራዘም የቀረበው የውሳኔ ሃሳብ በአብላጫ ድምጽ አጸደቀ።

ስድስተኛውን ብሔራዊ ምርጫ ለማራዘም የቀረበ የውሳኔ ሃሳብ ላይ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ባደረገው ውይይት የውሳኔ ሃሳቡን ተቀብሎ በ114 ድጋፍ፣ በአራት ተቃውሞ እና በአንድ ድምጸ ተዓቅቦ አጽድቋል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት በአምስተኛ የፓርላማ ዘመን አምስተኛ አመት ሁለተኛ መደበኛ ስብሰባው ላይ ስድስተኛውን ብሔራዊ ምርጫ ለማራዘም የምክር ቤቱ የህገ መንግስት ትርጉምና የማንነት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የውሳኔ ሃሳብ አቅርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሺኙ ስጋት ሆኖ እስካለበት ድረስ የሁሉም ምክር ቤቶች ስልጣን እንዲቀጥል ወስኗል።

እንዲሁም ወረርሽኙ ስጋት አለመሆኑን አለም ዓቀፍ የጤና ተቋማት ማረጋገጫ ከሰጡ በኋላ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይህንኑ ካጸደቀ በኋላ ከ9 ወር እስከ አንድ ዓመት ባለ ጊዜ ውስጥ ምርጫ ይካሄድ የሚለው ሃሳብ ላይ ነው ውሳኔ ያሳለፈው።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት የህገ-መንግስት ትርጉምና የማንነት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጸሐፊ ወርቁ አዳሙ እንዳቀረቡት፤ ህገ-መንግስት የመተርጎም ስልጣን ለፌደሬሽን ምክር ቤት እንዲሰጥ የተደረገበት ዋና ምክንያት ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤቶች የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች መሆናቸው ነው።

ጉዳዩ በመነሻነት ለህገ-መንግስት አጣሪ ጉባዔ ሊቀርብ የቻለው ብሔራዊ ምርጫ በሚካሄድበት የጊዜ ማዕቀፍ ውስጥ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከሰትና ወረርሽኙን ለመከላከል ለመቆጣጠርና የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ እንደሆነ አቶ ወርቁ ተናግረዋል፡፡

የህገ-መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ለቀረበለት የህገ-መንግስት ትርጉም ጥያቄ የውሳኔ ሃሳብ ከመስጠቱ በፊት ከ34 ግለሰቦችና ተቋማት 22 የሙያ አስተያየቶች በጽሁፍ ተቀብሎ በመዳሰስ በግብኣትነት ስለመጠቀሙም አስረድተዋል፡፡

ሶስት መድረኮችን በተለያዩ ጊዜያቶች በማዘጋጀት ከኢትዮጵያ የህግ ባለሙያዎችና ጠበቆች ማህበር ህገ-መንግስቱ በሚቀርብበትና በሚፀድቅበት ወቅት ተሳትፎ ከነበራቸው 10 ከፍተኛ ባለሙያዎች ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ከጤና ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት፣ ከጤና ባለሙያዎች ማህበርና ከኮቪድ-19 የሳይንስ አማካሪ ካውንስል የመጣውን መረጃ እንደ ማመሳከሪያነት ስለመጠቀማቸውም አብራርተዋል፡፡

ሂደቱም በተለያዩ አገር አቀፍ ሚዲዎች በቀጥታ ስርጭት ጭምር መተላለፉን አቶ ወርቁ ገልፀዋል፡፡

ብሔራዊ ምርጫው በተያዘለት ዓመት መካሄድ እንዳለበት በመንግስት በኩል ቁርጠኝነት እንደነበር ያወሱት የኮሚቴው ጸሐፊ፤ ጉዳዩን አስመልክቶ በልዩ ልዩ መድረኮች ለሚመለከታቸው አካላት፣ ለህዝብ፣ ለተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ጉዳዩ ለሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ግልፅ ሲያደርግ መቆየቱን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም