የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር ፓርቲ አመራር አባላት አዲስ አበባ ገቡ

4734

አዲስ አበባ ሰኔ 30/2010 በዶክተር አረጋዊ በርሄ የሚመራውና በውጭ ሀገር የፖለቲካ ትግል ያካሄድ የነበረው “የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር ፓርቲ”  ትግሉን በሰላማዊ መንገድ በሀገር ውስጥ ለማካሄድ በመወሰን ዛሬ አዲስ አበባ ገብቷል።

የፓርቲው አባላት ቡድን ዛሬ አዲስ አበባ ሲገባ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ሚኒስትር ዴኤታ  አቶ ካሳሁን ጎፌ እና ሌሎች የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ በመገኘት ተቀብለውታል።

ዶክተር አረጋዊ በዚሁ ወቅት በሰጡት መግለጫ ፓርቲያቸው ትግሉን በሀገር ውስጥ ለማካሄድ ወደሀገር ቤት የተመለሰው በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የተጀመረውን የዴሞክራሲና የአንድነት የለውጥ ሂደት በመደገፍ መሆኑን ተናግረዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አመራር የተጀመሩት እነዚህን የለውጥ እንቅስቃሴዎች በማጠናከር ሀገሪቱን ወደተሻለ ደረጃ ማሳደግ እንዲቻል የሀገሪቱ ጉዳይ የሚመለከተው ሁሉ  በጋራ መስራት እንዳለበትም አሳስበዋል።

ፓርቲው በውጭ ሀገር ሆኖ ለረጅም ዓመታት ለኢትዮዽያዊነት መንፈስ ሲታገል የቆየ መሆኑን የጠቆሙት ዶክተር አረጋዊ በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ ዴሞክራሲን እና አንድነትን ለማጠናከር የተጀመረው እንቅስቃሴ ከግብ እንዲደርስ ፓርቲያቸው ከሁሉም ጋር በጋራ ለመስራት መዘጋጀቱን አስታውቀዋል።

ዶክተር አረጋዊ እንደሚሉት በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የሚታየውን የለውጥ ሂደት የትግራይ ህዝብም የሚደግፈው በመሆኑ ከሌሎች ህዝቦች ጋር አብሮ ይሰራል።

የትግራይ ህዝብን በተመለከተ ከአንዳንድ አካላት የሚደመጠውን አፍራሽ አስተያየት ሁሉም ኢትዮጵያዊያን በአንድነት  እንዲታገሉት ጥሪ አስተላልፈዋል።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ካሳሁን ጎፌ በበኩላቸው መንግስት በሰላማዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎችን ይደግፋል ብለዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሀገሪቱ ቀጣይ እድገት መሳካት ከመንግስት ጋር  በጋራ እንዲሰሩም ጥሪ አቅርበዋል።

ለኢትዮዽያ እድገትና አንድነት ተቆርቋሪ የሆኑ እንደ ዶክተር አረጋዊ በርሄ ያሉ ምሁራን ወደ ኢትዮዽያ መምጣታቸው ለተጀመረው አዲስ ለውጥ ጠቃሚ መሆኑንም አቶ ካሳሁን ተናግረዋል።

ዶክተር አረጋዊ በርሄ የህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ (ህወሃት) መስራቾች መካከል አንዱ ነበሩ።