የአፈ ጉባኤዋ መልቀቅ በነገው የምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ ምንም አይነት ተፅእኖ የለውም – የምክር ቤቱ ምክትል አፈጉባኤ

387

አዲስ አበባ፣ ሰኔ2/2012(ኢዜአ) የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ የነበሩት የስራ መልቀቂያ ማስገባታቸው በነገው እለት በሚካሔደው ጉባኤ ላይ ምንም አይነት ተጽእኖ የሌለው መሆኑን ምክትል አፈጉባኤው ገለጹ።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አምስተኛ ዓመት ሁለተኛ ጉባኤውን በነገው እለት ይካሄዳል።

የምክር ቤቱ ምክት አፈ ጉባኤ አቶ መሐመድ ረሽድ ለኢዜአ እንደገለጹት በነገው ጉባኤ የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ የነበሩት መልቀቂያ ማስገባታቸው የሚፈጥረው ክፍተት አይኖርም።

አፈ ጉባኤዋ ከአንድ ሳምንት በፊት ለአባላቱ የስብሰባውን ጥሪ ያስተላለፉ ቢሆንም ከዚህ አስቀድሞ በገዛ ፈቃዳቸው ስራቸውን መልቀቃቸው ስብሰባው ላይ ምንም አይነት ተፅእኖ አያሳድርም ብለዋል።

የምክር ቤቱ አባላት የነገውን ስብሰባ በምክር ቤቱ ደንብ መሰረት የሚያካሒዱ መሆኑን አቶ መሐመድ ጠቁመዋል።

“አፈ ጉባኤዋ በደል ደርሶብኛል” እያሉ በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ያስተላለፉት መልእክት በስራ ላይ በነበሩበት ወቅት ያላነሱትና እንደ ኃላፊም ጥያቄ ያላቀረቡበት መሆኑንም አብራርተዋል።

አፈ ጉባኤዋ ስራቸውን መልቀቅ ካስፈለጋቸው በአግባቡና በአካል ቀርበው ማድረግ ሲገባቸው ይሕንን አለማድረጋቸውና ወደ ክልሉ ለስራ በሔዱበት በሚዲያ ማሳወቃቸው ተገቢ አለመሆኑንም ገልፀዋል።

አፈ ጉባኤዋ የሚሊዮን ህዝቦች ወኪል ስለነበሩ ሕዝብን በማክበር የተጣለባቸውን ሃላፊነት በአግባቡ መወጣት ይገባቸውም ነበር ብለዋል።

ሃላፊዋ በገዛ ፈቃዳቸው ስራቸውን ቢለቁም ሕገ መንግስቱ ባስቀመጠው አሰራር በምክትል አፈጉባኤ እየተመራ ምክር ቤቱ ስራውን እንደሚያከናውን ጠቅሰዋል።የፌዴሬሽን ምክር ቤት ነገ በሶስት የተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ይወያያል ተብሎ ይጠበቃል።