የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ በወረርሽኙ መከላከል ዙሪያ ከትግራይ ግብረ ኃይል ጋር ተወያዩ

54

መቀሌ፣ ሰኔ 2/2012 (ኢዜአ ) የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ በወረርሽኙ መከላከል ዙሪያ ከትግራይ ክልል ኮሮና ቫይረስ መከለከል ግብረ ኃይል ጋር ዛሬ በመቀሌ ከተማ ተወያዩ።

ክልሉ  ወረርሽኙን ለመከላከል በመግቢያ በሮችና ስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች ጫና ስላለበት ከፌዴራል መንግሥት ድጋፍ እንደሚሻ ተመልክቷል።

ሚኒስትሯ ከውይይቱ በኋላ ለጋዜጠኞች እንዳሉት ክልሉ በሚዋሰኑባቸው መግቢያ በሮች እያደረገ ያለውን የማቆያ ማዕከላት ማስፋት ሥራ ጠንካራ ነው።

ሆኖም ሥራው ከፍተኛ በጀትና የሰለጠነ የሰው ኃይል የሚጠይቅ በመሆኑ የፌዴራል መንግሥት ድጋፍ እንደሚያስፈልግ መገንዘባቸውን ተናግረዋል።

በመግቢያ በሮች አካባቢ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የመከላከል ሥራ የአንድ ክልል ብቻ ሳይሆን የሀገርና የዓለም አቀፍ ትብብር የሚፈልግ ነው ብለዋል።

ክልሉ ከውጭ በሚመለሱ ዜጎችና ስደተኞች ጫና እንዳለበት በውይይቱ  በመነሳቱ ለቀጣይ ትኩረት እንዲሰጠው ያግዛል ብለዋል።

በዚህም ችግሮቹ በማየት ለቀጣይ ትኩረት እንደሚደረግ ዶክተር ሊያ ገልጸዋል።

እስካሁን ለኮሮና ቫይረስ መከላከል የሚውል በጀት የሚደለደለው በሕዝብ ብዛት ቀመር መሆኑን ጠቅሰው ከአሁን በኋላ  ክልሎች ከበሽታው ተገላጭነታቸውና ጫና ጋር ታይቶ ትኩረት ተደርጎ ይሰራል ብለዋል።

የኮሮና መመሪመሪያ ላባላቶሪ ማዕከላት የማስፋቱ ሥራ ክልሉ የአቅም ችግር እንዳለበት መረዳታቸውን የተናገሩት ዶክተር ሊያ በቀጣይ ችግሩን ለማቃለል ሚኒስቴሩ የባለሙያ ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል ።

ከክልሉ ጤና ቢሮ ጋር በቅንጅት እንደሚሰሩም አመልክተዋል።

በክልሉ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ለመከላከል እያደረገ ያለው ቁጥጥርና ክትትል አበረታች መሆኑን  ጠቅሰው በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ መለስ ካምፓስ የኮሮና መከላከል ሕክምና መስጫ ማዕከል እየተከናወነ ባለው ሥራ መደሰታቸውን ተናግረዋል።

ሚኒስትሯ ከክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ደብረጽዮን እና ከንግድ፣ ኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አብረሃም ተከስተ ጋር ቫይረሱን ለመከላከል ባጋጠሙ ችግሮችና መፍትሔው ዙሪያ መወያየታቸውንም ጠቁመዋል።

የክልሉ ኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል ቴክኒክ  ኮሚቴ አስተባባሪና  የጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሓጎስ በበኩላቸው ቫይረሱን ለመከላከል በሚያጋጥሙ ችግሮች እና ሲከናወኑ በቆዩ ሥራዎች ላይ መወያየታቸውን ገልጸዋል።

የላብራቶሪ ባለሙያዎች፣ በጀት፤ የሕክምና የቁሳቁስ እጥረትና ሌሎች ቫይረሱን ለመከላከል የሚጠቅሙ ግብአቶች ችግር እንዳለ ከሚኒስትሯ ጋር በተወያዩበት ወቅት ማንሳታቸውን ጠቅሰዋል።

ክልሉ እስካሁን 34 ሚሊዮን ብር በፌዴራል መንግሥት ድጋፍ  እንደተደረገላቸው የተናገሩት ዶክተር ሓጎስ ይህም 17 ሚሊዮን ብር በጥሬ ገንዘብ ቀሪው ደግሞ በቁሳቁስ መሆኑን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም