የአካባቢያችንን ሰላም በመጠበቅ ሀገራዊ ለውጡን እናስቀጥላለን

70
ጋምቤላ ሰኔ 30/2010 የአካባቢያቸውንን ሰላም በመጠበቅ በሀገሪቱ እየታየ ያለውን ሀገራዊ ለወጥ ለማስቀጠል ጠንክረው እንደሚሰሩ የጋምቤላ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ። የከተማው ነዋሪዎች በክልሉ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ትናንት ውይይት አካሄደዋል። ነዋሪዎቹ በወቅቱ በሰጡት አስተያየት የአካባቢያቸውን ሰላም ነቅተው በመጠበቅ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እየመጡ ያሉትን ለውጦች ዳር ለማድረስ እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል ። ከተሳታፊዎች መካከል አቶ ኃይለማሪያም ተክለማሪያም በሰጡት አስተያየት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚያራምዷቸውን ሰላም፣ ፍቅርና አንድነት ለማጠናከር በንቃት እንደሚሰሩ ተናግረዋል። በሀገሪቱ እየታዩ ያሉ ለውጦች ያልተዋጠላቸው ጥቂት ፀረ- ሰላም ኃይሎች የፀጥታ ችግር እንዳይፈጥሩ ከመንግስት ጎን በመሰለፍ ለመመከት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል። “ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክትር አብይ አህመድ ወደ ከፋ የሰላም ቀውስ ልትገባ የነበረችውን ሀገር ከችግር ያወጡ ጠንካራ መሪ ናቸው'' ያሉት ደግሞ ሌለው የከተማው ነዋሪ አቶ ዘመድአገኘሁ ጋረድ ናችው። "በጠቅላይ ሚኒስትሩ እየመጡ ያሉ ለውጦችን የማይደገፉ ኃይሎችን በተደረጀ መልኩ መጠበቅ ይገባል " ብለዋል ። ሌላው የከተማው ነዋሪ አቶ ኡሞድ ኝጎሪ በሰጡት አስተያየት ጠቅላይ ሚነስትር ዶክትር አብይ አህመድ "ሀገሪቱ ከነበረችበት ችግር እንድትወጣ ብቻ ሳይሆን በአጭር ጊዜ ውስጥ ባከናወኗቸው የሰላም፣ የእርቅና የአንድነት ተግባር የኢትዮጵያ ህዝብ እፎይታ አግኝቷል" ብለዋል። "እየተዘመረ ያለውን የሰላም፣ የፍቅር፣ የአንድነትና የመግባባት ሂደት ወደ ኋላ ለመቀልበስ የሚሞክሩ ፀረ- ሰላም ኃይሎችን ነቅቶ በመጠበቅ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የመጡትን ለውጦች ዳር ለማደረስ መስራት ይገባል" ያሉት ደግሞ አቶ ደነቀ አቢ ናቸው። የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሰናይ አኩዎር በወቅቱ እንደተናገሩት ኢህአዲግ በጥልቅ ታድሶ ግምገማ ያስቀመጣቸውን አቅጣጫዎች ዶክትር አብይ አህመድ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ተግባር በመለወጣቸው ሀገሪቱ ወደ ትክክለኛ የለውጥ ጉዞ ገብታለች። ይሁንና የለውጥ ጉዞው ያልተዋጠላቸው ቡድኖች በክልሉም ሆነ በሀገሪቱ የሰላም ችግር እንዲፈጠር የተለያዩ ሙከራዎችን እያካሄዱ እንደሚገኙ ጠቁመዋል። የክልሉ ህዝብ አንድነቱን ጠብቆ የፀረ- ሰላም ኃይሎችን ሴራ ለማክሸፍ መስራት እንዳለበት አስገንዝበዋል። በክልሉ ሰሞኑን የተለያዩ ውዥንብሮችን በመንዛት የሰላም ችግር ለመፈጠር በሞከሩ ኃይሎች ላይ የክልሉ መንግስት ክትትል በማድግ እርምጃ እንደሚወስድ አስገንዝበዋል ። ለስኬታማነቱ የህዝቡ ትብብር ሊጠናከር እንደሚገባ ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አስታውቀዋል ።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም