በዋግ ኽምራ የዝናብ እጥረት ለመከላከል የእርጥበት ዕቀባ ሥራ ይከናወናል

52

ሰቆጣ፣ ሰኔ 2/2012 (ኢዜአ) በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር በዘንድሮው የመኽር አዝመራ በ55 ሺህ ሔክታር መሬት ላይ የእርጥበት ዕቀባ ሥራ ለማከናወን ዝግጅት መደረጉን የብሔረሰብ አስተዳደሩ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።

የመምሪያው የሰብል ልማትና ጥበቃ ቡድን መሪ አቶ በዛብህ ጌታሁን ለኢዜአ እንዳሉት በዘንድሮው የመኸር አዝመራ በአርሶ አደሩ ማሣ ላይ እርጠበትን ማቀብ የሚችሉ ዘዴዎችን ለመጠቀም ዝግጅት ተደርጓል።

ብሔረሰብ አስተዳደሩ የዝናብ አጠር አካባቢ በመሆኑ የክረምት ዝናብ በሚቆራረጥበትና ቀድሞ በሚወጣበት ጊዜ በአርሶ አደሩ ሰብል ላይ ጉዳት እንዳይደርስ በማሣ ላይ እርጥበትን የማቆየት ዘዴ ይተገበራል።

በመኸር እርሻ መታረስ ከሚችለው 120 ሺህ 638 ሔክታር መሬት ውስጥ በ55 ሺህ ሔክታር መሬቱ ላይ እርጥበትን ማቀብ የሚያስችሉ ዘዴዎች ለማከናወን እየተሰራ ነው።

የእርጥበት ዕቀባ ሥራውም በ47 ሺህ አርሶ አደሮች የእርሻ ማሣ ውስጥና ዳርቻ ላይ የሚከናወን መሆኑን አመልክተዋል።

የዕቀባ ሥራውም በማሣ ውስጥ ቁፋሮ፣ የማሣ አናት አነስተኛ ኩሬ፣ ጎርፍ መቀልበሻና ደጋፊ መስኖ መሥራት የሚሉ አማራጮች በአርሶ አደሩ ማሣ ላይ ተግባራዊ እንደሚደረግ ገልጸዋል።

ባለፈው ዓመትም 57 ሺህ ሔክታር መሬት በእርጥበት ዕቀባ በማልማት የሰብል ምርታማነትን ማሻሻል እንደተቻለ ገልጸዋል።

የእርጥበት ዕቀባ ሥራ የሰብል ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ዓይነተኛ አማራጭ ነው ያሉት አቶ በዛብህ በተለይም አርሶ አደሩ ጉልበቱን ሳይሰስት የእርጥበት ዕቀባ ሥራውን እንዲያከናውን መክረዋል።

በሰቆጣ ዙሪያ ወረዳ የወለህ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ቢሰጥ ሲሣይ እንዳሉት በግማሽ ሔክታር መሬታቸው ላይ አነስተኛ ጉድጓድ በመቆፈር እርጥበትን ለማቀብ እየሰሩ መቆየታቸውን ተናግረዋል።

በዚህ ክረምትም ፈጥነው የሚደርሱ ሰብሎችን ማዳበሪያን በመጠቀም ለመዝራት በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ጠቅሰው በማሣቸው ዳርቻ ላይ እርጥበትን ማቀብ የሚችሉ አነስተኛ ጉድጓዶችን እያዘጋጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በዝቋላ ወረዳ የ01 ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ሚሰነ ጎሹ በበኩላቸው ባለፈው ዓመት በማሣቸው ዳርቻ የሚያልፈውን ጎርፍ ጠልፈው ወደ ማሣቸው በማስገባት የተሻለ የማሽላ ምርት ማግኘት እንደቻሉ አስታውሰዋል።

በዘንድሮው ዓመትም እንደባለፈው ዓመት ሁሉ ውኃን ማሰባሰብ የሚችሉ ጉድጓዶችን ለመቆፈር በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር በመኽር አዝመራው ከአንድ ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱን ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም