በጎባ ከተማ ወጣቶች ከጥቃቅንና አነስተኛ ወደ ሌሎች የኢንቨስትመንት አማራጮች እየተሸጋገሩ ነው

525

ጎባ፣ ሰኔ 02/2012 (ኢዜአ) በባሌ ዞን ጎባ ከተማ በጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፍ የተሰማሩ ወጣቶች ባስመዘገቡት ውጤት ወደ ሌሎች የኢንቨስትመንት አማራጮች እየተሸጋገሩ መሆናቸውን ገለጹ፡፡

የዞኑ የኢንተርፕራይዝ ልማትና ኢንዱስትሪ ጽህፈት ቤት በበኩሉ ዘንድሮ ከ28 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ 32 ማህበራት ወደ ኢንቨስትመንት እንደተሸጋገሩ ተመልክቷል፡፡

ከወጣቶቹ መካከል ደረጀ ደጀኔ ለኢዜአ እንዳለው ከሌሎች ሶስት ጓደኞቹ ጋር ከኦሮሚያ ብድርና ቁጠባ ተቋም በወሰዱት 25ሺህ ብር መነሻ ካፒታል  በቤትና ቢሮ ዕቃዎች ምርት ስራ ላይ ተሰማርተዋል።

ባለፉት አራት ዓመታት ባደረጉት የስራ እንቅስቃሴ ከ20 ለሚበልጡ ሌሎች ወጣቶች የስራ እድል ከመፍጠራቸውም ባሻገር ሶስት ሚሊዮን 500ሺህ  ብር ካፒታል ማፍራት ችለዋል።

በዚህም  ወደ ሆቴል ኢንቨስትመንት ለመሸጋገር ቦታ ተረክበው ቅድመ ሁኔታዎችን በማመቻቸት ላይ እንደሚገኙ ወጣት ደረጀ ተናግረዋል፡፡

ደረጀ ሌሎች ወጣቶችም አሁን በተፈጠረው ምቹ ሁኔታ ሁሉ ስራን ሳይንቁ ራሳቸውን መቀየር እንደሚችሉ ተሞክሯቸውን በማሳያነት አመላክቷል፡፡ 

መንግሥት በፈጠረላቸው  ምቹ ሁኔታ ተጠቅመው በዶሮ እርባታ በመሰማራት ከቤተሰብ ጠባቂነት  እንደተላቀቁና ለሌሎች ወጣቶችም የስራ እድል ማመቻቸት እንደቻሉ የተናገረችው ደግሞ ወጣት እነህንዲያ አብዱልቃድር ናት።

ከሁለት ጓደኞቿ  ጋር በመደራጀት ባለፉት ሶስት ዓመታት ባደረጉት የስራ እንቅስቃሴ ከአንድ ሚሊዮን 600ሺህ  ብር በላይ ካፒታል በማስመዝገብ ወደ ኢንቨስትመንት መሸጋገራቸውን ገልጻለች።

በአንድ ጊዜ እስከ አራት ሺህ ጫጩቶችን በማስፈልፈል እየተንከባከቡ  ለገበያ ማቅረብ በማቅረብ ውጤታማ መሆን ችለዋል።

በቀጣይም ባለው የኢንቨስትመንት አማራጭ በሚያረቡት ዶሮዎች ላይ እሴት በመጨመር ለገበያ ለማቅረብ የልማት መሬት ከመንግስት ማግኘታቸውን  ወጣት እነህንዲያ ገልጻለች፡፡

የጎባ ከተማ የኢንተርፕራይዝ ልማትና ኢንዱስትሪ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብዱልባሪ ኢብራሂም በበኩላቸው ” ከተማ አስተዳደሩ ወጣቶች በተለያዩ የስራ አማራጮች ተደራጅተው እራሳቸውን እንዲቀይሩ በትኩረት እየሰራ ነው “ብለዋል፡፡

በተለይም በከተማዋ ባለፉት ዓመታት  በጥቃቅንና አነስተኛ ማህበራት ተደራጅተው የስራ እድል ከተፈጠረላቸው ወጣቶች መካከል ከ13 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል በማስመዝገብ ለሌሎች ወጣቶች የስራ እድል አስገኝተው  ወደ ሌሎች የኢንቨስትመንት አማራጮች የተሸጋገሩ እንዳሉ አመልክተዋል።

አስተዳደሩ የስራ አጥነት ችግር ለመፍታት  ከመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲና ሌሎች መንግስታዊ ተቋማት ጋር በመቀናጀት ከ500 የሚበልጡ ወጣቶች በቋሚነት የስራ እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉንም  ገልጸዋል።

በባሌ ዞን  ባለፉት አስር ወራት በጥቃቅንና አነስተኛ ማህበራት የተደራጁ ከ32ሺህ የሚበልጡ ወጣቶች ቋሚ  የስራ እድል የተፈጠረላቸው መሆኑን የገለጹት ደግሞ የዞኑ የኢንተርፕራይዝ ልማትና ኢንዱስትሪ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጫልቺሳ ዘውዴ ናቸው።

ከተፈጠረላቸው  የሥራ ዘርፎች መካከልም ግብርና፣ የዶሮ እርባታ፣ እንጨትና ብረታ ብረት ሥራ፣ ማኑፋክቸሪንግ፣ ኮንስትራክሽን፣ የከተማ ግብርና፣ ንግድ እና የሥራ ቅጥር ይገኙበታል፡፡

በዞኑ ባለፉት ዓመታት በተለያዩ 32 አነስተኛና ጥቃቅን ማህበራት ስር በመደራጀት ከ28 ሚሊዮን ብር ባላይ ካፒታል በማስመዝገብ ውጤታማ የሆኑ 165 ወጣቶች ወደ ኢንቨስትመንት መሸጋገራቸውን አመልክተዋል፡፡ 

በባሌ ዞን በበጀት ዓመቱ  40ሺህ ለሚበልጡ ወጣቶች የስራ እድል ለመፍጠር ታቅዶ እየተሰራ መሆኑንም ተመልክቷል፡፡