በዲላ ከተማ የአካል ብቃት የስፖርት እንቅስቃሴ ስልጠና ተጀመረ

121

ዲላ ሰኔ 1/2012(ኢዜአ) በጌዴኦ ዞን ዲላ ከተማ ሁሉ አቀፍ የአካል ብቃት የስፖርት እንቅስቃሴ ስልጠና ተጀመረ።

የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ዜጎች በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ ለረዥም ሰዓታት ቤት መቀመጣቸው ለአእምሮ ጭንቀትና ተጓዳኝ በሽታዎች እንዳያጋልጣቸው የሚረዳ መሆኑ ተመልክቷል።

የከተማዋ  አስተዳደር  ባህል ቱሪዝምና ስፖርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ እንዳለ ቦጋለ  እንደገለጹት  

ርቀትን ጠብቆ የሚካሄድ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በሽታን  የመከላከል  አቅምን በማሳደግ ረገድ የጎላ ጠቀሜታ አለው።

ለኮሮና ቫይረስ አጋላጭ በማይሆን የተቀናጀ አግባብ ጽህፈት ቤቱ  ከዲላ ዩኒቨርሲቲ ጋር  ስልጠና መስጠት መጀመራቸውን ገልጸዋል።

በስልጠናው በከተማዋ  በተለይም በጋራ መኖሪያ ቤቶችና ሰዎች ተጠጋግተው በሚኖሩ መንደሮች የሚገኙ ከ300 በላይ ነዋሪዎች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ ብለዋል።

ስልጠናው በቀጣይም በሳይንሳዊ አቀራረብ በዘርፉ በሰለጠኑ ምሁራን በሳምንት ለሶስት ቀናት እንደሚሰጥ ተመልክቷል።

ዜጎች በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ ለረዥም ሰዓታት ቤት መቀመጣቸው ለአእምሮ ጭንቀትና ተጓዳኝ በሽታዎች እንዳያጋልጣቸው የአካል ብቃት እንቅስቃሴ  እንደሚጠቅማቸው የተናገሩት ደግሞ በዲላ ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ሳይንስ መምህር ዐቢይ ረጋሳ ናቸው።

ወረርሽኙን ለመከላከል እንዲያግዝ   እሳቸውን ጨምሮ ስምንት የስፖርት መምህራን በበጎ ፍቃድኝነት በአካል ብቃት እንቅስቃሴ ያላቸውን እውቀት ለማካፈል መነሳታቸውን  ገልጸዋል።

በስልጠናው እየተሳተፉ ካሉት መካከል ወጣት ምናሴ ወጋዬሁ ስለአካል ብቃት እንቅስቃሴ በተግባር የተደገፈ ስልጠና መዘጋጀቱ በኮሮና ምክንያት የሚመጣውን ድብርት በመቀነስ ቀኑን ሙሉ ንቁ ሆኖ ለማሳለፍ እንደሚያግዘው በመረዳት መሳተፉን ተናግሯል።

በተለይ ስልጠናው የሚሰጠው በዘርፉ ምሁራን በመሆኑ እራሱንና ቤተሰቡን ከቫይረሱ በመጠበቅ የአካል ብቃት እንቅስቃሴው  እንደሚቀጥልበትም ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም