በኢትዮጵያ የምግብ ጥራት ማረጋገጫ አክሪዲቴሽን ዝቅተኛ ነው

50

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 1/2012 ( ኢዜአ) በኢትዮጵያ የላቀ የምግብ ጥራትን ለማስጠበቅ በምግብ ሰንሰለቶችና የአሰራር ሂደቶች የሚደረገው የጥራት ማረጋገጫ አክሪዲቴሽን ዝቅተኛ መሆኑ ተገለጸ።

ብሔራዊ አክሪዲቴሽን ጽህፈት ቤት “አክሬዲቴሽን የምግብ ደህንነትን ያሳድጋል” በሚል መሪ ሀሳብ ነገ የሚከበረውን 10ኛውን የዓለም አክሬዲቴሽን ቀን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።

የጽህፈት ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ አርዓያ ፍስሃ በመግለጫቸው እንዳሉት የምግብ ደህንነትና የላቀ ጥራት ማስጠበቅ ከሚበቅልበት አፈር ጀምሮ እስከ ተጠቃሚው ድረስ ያለውን ያካትታል።

ነገር ግን በኢትዮጵያ የምግብ ጥራትና ደህንነትን ለማስጠበቅ ከአፈር ምንነት፣ ከዘር፣ ከያዘው ንጥረ ነገርና ከፀረ-አረም፣ ከማከማቻና ማጓጓዣ እስከ ተጠቃሚው ላሉት ሰንሰለቶች የሚሰጠው ትኩረት ዝቅተኛ እንደሆነ ተናግረዋል።

በዘርፉ የተሰማሩ ግለሰቦች፣ ድርጅቶችና ሙያተኞች እንዲሁም ላኪዎች የተቀናጀ የአክሪዲቴሽን አሰራሮችን ለመከተል ያላቸው ፍላጎት ዝቅተኛ መሆኑንም ነው የጠቆሙት።

እንደ በርበሬና ስጋ ያሉ ምግብ ነክ ወጪ ምርቶች በጥራት ችግር ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነታቸው ላይ ጥያቄ የሚነሳው የደረጃ መዳቢ፣ የተስማሚነትና የአክሪዲቴሽን አሰራር የቅንጅት ክፍተት በመኖሩ እንደሆነም አክለዋል።

የዓለም የንግድ ድርጅት እ.አ.አ በ2019 ባካሄደው ጥናት 30 በመቶ የንግድ ስምምነቶች፣ 12 በመቶ የቴክኒክ ምርመራዎችና 10 በመቶ ሌሎች የንግድ መስፈርቶች በምግብ አክሪዲቴሽን ላይ ማጠንጠናቸውን አንስተዋል።  

ይህም ከ52 በመቶ በላይ የዓለም አቀፍ ምግብ-ነክ ንግድ መስፈርቶች ከአክሬዲቴሽን ጋር የተያያዙ መናቸውን ያሳያል።

የዓለም የምግብ ድርጅትም እ.አ.አ በ2019 በዓለም ላይ 420 ሺህ ሰዎች በምግብ ጥራት ችግር መሞታቸውንና ከ300 ሺህ በላይ የሚሆኑት ሕጻናት እንደሆኑ አመልክቷል።

የአክሪዲቴሽን አሠራሮችን መተግበር የምግብ ጥራት ያስጠብቃል፤ ተወዳዳሪነታቸውንም ያሰፋል ያሉት አቶ አርዓያ በዘርፉ የተሰማሩ አካላት በዚህ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል።

የዘርፉ አክሪዲቴሽን ተጠቃሚዎች ዝቅተኛ መሆናቸውን የገለጸው ጽህፈት ቤቱ ከዓለም የአክሪዲቴሽን ቀን መከበር ጋር ምግብ ነክ ምርትና አገልግሎቶችን ለመፈተሽ ተዘጋጅቻለሁ ብሏል።

አክሬዲቴሽን የምርትና አገልግሎቶችን ጥራት የተቀመጡ መስፈርቶችን /ፓራሜትሮች/ መሰረት በማድረግ የሚሰጥ የጥራት ማረጋገጫ አገልግሎት ነው።

ተገልጋዮች የምርት ወይም የአገልግሎት ጥራት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት የሚወስዱት ባቀረቧቸው መስፈርቶች ሲሆን 6 ወር መጠበቅ እንደሚኖርባቸውም ተገልጿል።

አሰራሩም በየስድስት ወሩ እየተገመገመ እስክ 4 ዓመት ተኩል ይቀጥላል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ አክሪዲቴሽን ጽህፈት ቤት ከ102 ዓለም አቀፍ የአክሪዲቴሽን ተቋማት አንዱ ሲሆን ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ መስፈርቶች ለ53 ድርጅቶች የምርትና አገልግሎት የጥራት ማረጋገጫ ሰጥቷል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም