መንግስት ኮሮናቫይረስን አስመልክቶ ለሕዝብ የደበቀው ምንም መረጃ የለም

183

አዲስ አበባ ሰኔ 1/2012(ኢዜአ) "መንግስት ኮሮናቫይረስን አስመልክቶ ለሕዝብ የደበቀው ምንም መረጃ የለም" ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ገለጹ። 

በመጪው ሐምሌ ኢትዮጵያ በቀን የምትመረምረው የሰው ቁጥር 14 ሺህ እንደሚደርስም አስታውቀዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት መሰበሰቢያ አዳራሽ እየተካሄደ ባለው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ልዩ ስብሰባ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ እየሰጡ ነው።

ከአባላቱ ከተነሱ ጥያቄዎች መካከል የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በጤና፣ በኢኮኖሚና ማህበራዊ መስኮች እያደረሰ ያለውን ጉዳት ለመቀነስ በመንግስት ምን አይነት እርምጃ እየተወሰደ ነው? የሚል ይገኝበታል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የኮሮናቫይረስ ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከሚረዱ መንገዶች አንዱ ቫይረሱን አስመልክቶ ለኅብረተሰቡ አስፈላጊውን መረጃ መስጠት አንዱ ነው ብለዋል።

ቫይረሱን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ለሚከወኑ ስራዎችን አስመልክቶ በተቋቋመው የሚኒስትሮች ኮሚቴ የተቀመጠው አቅጣጫም መረጃዎችን ለህብረተሰቡ ግልጽ ማቅረብ እንደሆነ ገልጸዋል።

እስካሁን ባለው ሁኔታ የኮሮናን ቫይረስ አስመልክቶ መንግስት የሚያውቀውን ነገር ያለምንም ድብብቆሽ ለሕዝብ ተደራሽ ማድረጉንም ተናግረዋል።

ምክንያቱም የሚፈለገውን መረጃ ለህብረተሰቡ አለመስጠት የቫይረሱን ስርጭት ከቁጥጥር ውጭ እንዲሆን ስለሚያደርገው፣ መንግስትም ያሉትን መረጃዎች ለህብረተሰቡ በአግባቡ እያቀረበ መሆኑን አስታውቀዋል

መረጃ ያለው፣ ያወቀና የገባው ሰው ቫይረሱን በተሻለ መልኩ መከላከል እንደሚችልም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያስረዱት።

በሌላ በኩል ከሶስት ወራት በፊት ወደ ደቡብ አፍሪካ ናሙና ልኮ የኮሮናቫይረስ ምርመራ ውጤት ከመቀበል ተነስቶ አሁን የላቦራቶሪ የመመርመር አቅም እያደገ መምጣቱን ነው የገለጹት።

በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በ31 የምርምራ ማዕከላት በቀን ስምንት ሺህ ሰው የመመርመር አቅም ላይ መደረሱን ጠቅሰዋል።

በተያዘው ወር ተጨማሪ 15 የምርመራ ማዕከላት ወደ ሥራ እንደሚገቡና በሐምሌም የመመርመር አቅሙ በቀን 14 ሺህ ሰው እንደሚደስርስም ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ ከደቡብ አፍሪካ፣ ጋና እና ሞሮኮ ቀጥላ ብዙ ሰው የመረመረች ቢሆንም፣ ከሕዝብ ብዛቷ አንጻር አነስተኛ በመሆኑ የምርመራ አቅምን የማሳደግ ሥራ ትኩረት ተሰጥቶት እየተከናወነ ነው ብለዋል።

አሁን ላይ 17 ሺህ 500 የኮሮናቫይረስ ታማሚዎችን ማስተናገድ የሚችሉ 54 የሕክምና ማዕከላት መዘጋጀታቸውንም ገልጸዋል።

የቫይረሱ ምልክት የታየባቸው 30 ሺህ ገደማ ሰዎች በለይቶ ማቆያ እንደሚገኙና፣ አቅም ለሌላቸው 45 ሺህ ኢትዮጵያዊያንም የለይቶ ማቆያ ማዕከላት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

ከመካከለኛው ምስራቅ ለሚመጡ ኢትዮጵያዊያንም አቅም በፈቀደ መልኩ ድጋፍ እየተደረገላቸው እንደሆነ ነው ያስረዱት።

በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱንና የከፋ ጊዜ ቢመጣም ለመከላከል የሚያስችል አቅም እየተገነባ መሆኑን ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹት።

ኮሮናቫይረስን ለመከላከል እየተገነባ ያለው አቅም በወባ፣ በካንሰርና በሌሎች በሽታዎችም መደገም እንዳለበትና ይህን ማድረግ ከተቻለ የብዙ ዜጎችን ሕይወት መታደግ እንደሚቻል ተናግረዋል።

መንግስት ኮሮናቫይረስን ለመከላከል አምስት ቢሊዮን ብር መድቦ እየተንቀሳቀሰ እንደሆነም አመልክተዋል።

ክልሎች ቫይረሱን ለመከላከል የሚያስችላቸውን አቅም እንዲገነቡ አንድ ቢሊዮን ብር የሚገመት የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉንም አንስተዋል።

በህብረተሰቡ ዘንድ ኮሮናቫይረስን ለመከላከል የሚያደርገው ጥንቃቄ መዘናጋት እንደሚስተዋልበት የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ህብረተሰቡ ተገቢውን የጥንቃቄ እርምጃ መውሰድ እንዳለበት አሳስበዋል።

በአጠቃላይ መንግስት የኮሮናቫይረስ በጤናው ሥርዓት ላይ ብቻ ሳይሆን በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሌሎች ዘርፎች የሚደርሰውን ተፅዕኖና ጉዳት ለመቀነስ የሚያስችል ተግባር እያከናወነ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም