ጅማ ዩኒቨርሲቲ ለአቶ ለማ መገርሳ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ሰጠ

88
ጅማ ሰኔ 30/2010 የጅማ ዩኒቨርሲቲ ለኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሳ የሰላምና ደህንነት የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ሰጠ። ዩኒቨርሲቲው ለፕሬዝዳንቱ የክብር ዶክትሬት ዲግሪውን የሰጠው በቅድመና ድህረ ምረቃ መርሀ ግብር ያሰለጠናቸውን 2ሺህ 982 ተማሪዎች ዛሬ ባስመረቀበት ወቅት ነው ። የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ፍቅሬ ለሜሳ በወቅቱ እንደገለፁት የዩኒቨርሲቲው ትምህርት ጉባኤ ሰኔ 20 ቀን 2010 አ.ም ባካሄደው ስብሰባ ፕሬዝዳንቱ የጥላቻ ግርዶሽን በማፍረስ፣ ከራስ ጥቅም ይልቅ ለማህበረሰብ ቅድሚያ በመስጠትና ስልጣንን ለህዝብ መገልገያነት በተግባር በማዋላቸው የክብር ዶክትሬት ዲግሪው እንዲሰጣቸው ወስኗል ። ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሳ በበኩላቸው ከዩኒቨርሲቲው የተበረከተላቸው የክብር ዶክትሬት ዲግሪ የሚጠብቃቸውን ከባድ ሀላፊነት ለመወጣት ጥንካሬ የሰጣቸው መሆኑን ገልፀዋል ። ተመራቂዎች በቀጣይ እራስንና ቤተሰብን የመምራት እንዲሁም ለአገር አስተዋፆ የማበርከት ድርብ ሀላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ፕሬዝዳንቱ አሳስበዋል ። ጅማ ዩኒቨርሲቲ ባለፈው ሳምንት በቅድመና ድህረ ምረቃ መርሀ ግብር 4ሺህ 783 ተማሪዎችን ማስመረቁ ይታወሳል ።            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም