በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ኮሮናን ለመከላከል የቤት ለቤት አሰሳው ተጠናክሮ እንደቀጠለ ነው

አሶሳ፣ ግንቦት 30/2012 (ኢዜአ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል የቤት ለቤት አሰሳው ተጠናክሮ መቀጠሉን የክልሉ ኮሮና መከላከል ዐብይ ግብረ ኃይል ገለጸ።

የግብረ ኃይሉ አባልና የጤና ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ፍሬሕይወት አበበ  በሰጡት መግለጫ እንዳሉት በክልሉ የቫይረሱን ሥርጭት ለመግታት የቤት ለቤት አሰሳው ተጠናክሮ የቀጠለው በጤና ባለሙያዎችና በጎ ፈቃደኞች የተደራጀ ቡድን ነው።

የቡድኑ ዋነኛ ተግባር የሰውነት ሙቀትና ሌሎችንም የጤና ምርመራዎች ማከናወን እንደሆነ ጠቅሰዋል።

ባለፈው አንድ ሣምንት በክልሉ ሦስት ዞኖች፣ አንድ ልዩ ወረዳና ከተማ አስተዳደር ቡድኑ 185 ሺህ ሰዎችን ተደራሽ ማድረግ ተችሏል።

ይህም ቡድኑ በሣምንቱ ያከናወነው፤ ተግባራዊ ለማድረግ ከያዘው ዕቅድ 75 በመቶ እንደሆነ ወይዘሮ ፍሬሕይወት በመግለጫቸው አብራርተዋል።

በቤት ለቤት አሰሳው ከ500 በላይ ሰዎች የሰውነት ሙቀታቸው ጨምሮ በመገኘቱ በተደረገላቸው ተጨማሪ የጤና ምርመራ የቲቢና ወባ በሽታ ምልክቶች እንደታየባቸው  አስረድተዋል።

በክልሉ ኅብረተሰቡ ዘንድ አካላዊ ርቀትን አለመጠበቅ ችግር አሁንም መቀጠሉ አሳሳቢ እንደሆነ ኃላፊዋ ጠቁመዋል።

ኅብረተሰቡ ኮሮናን ለመከላከል የሚተላለፉ መመሪያዎችን በሚገባ በመተግበር ወረርሽኙን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት እንዲደግፍ ወይዘሮ ፍሬሕይወት ጥሪ አቅርበዋል።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ቀደም ብለው በተካሄዱ ምርመራዎች የኮሮና ቫይረስ የተገኘባቸው ሰዎች እንዳሉ የጤና ሚኒስቴር ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም