በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ከ50 ሺህ በላይ ወጣቶች በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ይሰማራሉ

70
ሰቆጣ ሰኔ 30/2010 በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ከ50 ሺህ በላይ ወጣቶች በክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ለማሰማራት ዝግጅት መደረጉን የዞኑ ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ አስታወቀ፡፡ የመምሪያው ኃላፊ አቶ አዲሴ በላይ ለኢዜአ እንደገለፁት በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች፣ ኮሌጆች፣ መለሰተኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚማሩ ተማሪዎችና ወጣቶች ይሳተፋሉ። ወጣቶቹ ሰቆጣ ከተማ አስተደደርን ጨምሮ በሁሉም ወረዳዎች ከሃምሌ 5 ቀን 2010 ጀምሮ ለተከታታይ ሁለት ወራት አገልግሎቱን እንደሚሰጡ ተናግረዋል፡፡ በተለይም “ብሄረሰብ አስተዳደሩ ዝናብ አጠር እንደመሆኑ መጠን የርጥበት እቀባ ስራ በአርሶ አደሩ ማሳ ላይ በስፋት ይሰራል'' ብለዋል፡፡ ለአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርት ይሰጣል ያሉት ኃላፊው በእናቶች እና  ህፃናት ጤንነት መጠበቅ ዙሪያም ወጣቶች በበጎ ፍቃድ አገልግሎቱ እንደሚሰማሩ ተናግረዋል፡፡ የበጎ ፈቃድ ስራውን በወቅቱ ለማስጀመርም ከሰኔ 25 ጀምሮ የበጎ ፈቃደኞች ምዝገባ እየተደረገ ሲሆን በአካባቢያቸው እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎችን እንዲጎበኙ ለማድረግ ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም አብራርተዋል። ተማሪ ግርማ ማሞ በሃዋሳ የ2ኛ አመት የግብርና ትምህርቱን አጠናቆ የእረፍት ጊዜውን በበጎ ፍቃድ አገልግሎት ለመሰማራት ዝግጁ መሆኑን ተናግሯል፡፡ በተለይም በዩኒቨርሲቲ ትምህርቱ ያገኘውን እውቀት በበጎ ፍቃድ አገልግሎት ወደ ተግባር ለመቀየር በግብርና ዘርፍ ለመሰማራት እንዳሰበ አስታውቋል። ሌላው በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የአራተኛ አመት የምህንድስና ተማሪ የሆነው ሀይለማርያም ፍቃዴ በበኩሉ ባለፉት 3 አመታት በክረምት በጎ ፍቃድ ተግባር መሳተፉን አስታውሷል። በበጎ ፈቃደኝነት በመሳተፉም የህሊና እርካታ እንደሚሰማው ገልፆ በዘንድሮው ክረምትም የማጠናከሪያ ትምህርት ለመስጠት መዘጋጀቱንም አስታውቋል። ባለፈው የክረምት ወቅት በዞኑ  62 ሺህ 551 ያህል በጎ ፍቃደኞችን በተለያዩ የልማት ስራዎች በማሳተፍ 4 ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ብር የሚገመት  አስተዋጽኦ ማበርከታቸው ታውቋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም