ከእጅ ንኪኪ ነፃ የሆነ ዘመናዊ የእጅ መታጠቢያ በምኒሊክ አደባባይ አገልግሎት እየሰጠ ነው

106

አዲስ፣ አበባ 30/2012 (ኢዜአ) ከእጅ ንኪኪና ጥግግት ነፃ የሆነ ዘመናዊ የእጅ መታጠቢያ በአዲስ አበባ ምኒሊክ አደባባይ አገልግሎት እየሰጠ ነው።

ሕዝብ በብዛት በሚንቀሳቀስበት በምኒሊክ አደባባይ ከእጅ ንኪኪና ጥግግት ነፃ የሆነ ዘመናዊ አዲስ የእጅ መታጠቢያ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል።

በኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከሰትን ተከትሎ የድርሻውን ለማበርከት ይህንን ዘመናዊ የእጅ መታጠቢያ እንደሰራ የፈጠራ ባለሙያው ታምሩ ካሣ ተናግሯል።

ዘመናዊው የእጅ ማስታጠቢያ በአሥር ቧንቧዎችና 20 ሺህ ሊትር ዉኃ በሚይዝ ታንከር በአንድ ሰዓት እስከ 1200 ሰዎችን በአንዴ ማስተናገድ ይችላል ብሏል።

120 ሺህ ብር ያህል ወጪ እንዳደረገበት የሚናገረው የፈጠራ ባለሙያው የእጅ መታጠቢያው ፈሳሽ ሣሙናና ዉኃ ራሱ ለክቶ የሚሰጥ በመሆኑ አንድ ሰው ለ20 ሰከንድ በሣሙና እጁን አሽቶ እስኪያለቀልቅ የዉኃ ብክነት እንደማይኖር ገልጿል።

ባለሙያው ታምሩ ካሣ አያይዞም ተጠቃሚዎች እጃቸውን በሚታጠቡበት ወቅት ፍሳሹ መሬት ላይ ስለማይፈስ አካባቢው ከብክለት የጸዳ በመሆኑ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን አመልክቷል።

ዉኃውንም በቀን ሁለት ጊዜ የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና ቁጥጥር ባለሥልጣን እንደሚያቀርብለት ገልጾ የፈሳሽ ሣሙና ደግሞ በጎፈቃደኛ የመርካቶ ነጋዴዎችን በመለመን እንደሚያገኝ የፈጠራ ባለሙያው አስታውቋል።

በአሁኑ ወቅት በቀን ሁለት ጊዜ በሥራ ሰዓት መግቢያና መውጪያ እስከ ምሽት ሁለት ሰዓት በአካባቢው ለሚተላለፈው ሕዝብ አገልግሎት በመስጠቱ ደስተኛ መሆኑንም ባለሙያው ገልጿል።

በአድቫንስድ ኤሌክትሮኒክስ ምሩቅ መሆኑን የሚናገረው ባለሙያው በኮቪድ-19 ወረርሽኝ የሚያዘው ቁጥር በየቀኑ እየጨመረ በመምጣቱ በብዛት የሕዝብ እንቅስቃሴ በሚታይባቸው አካባቢዎች የእጅ ማስታጠብ እንዲስፋፋ ዓላማው መሆኑን ገልጿል።

የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላትና በጎ ፈቃደኞች ድጋፍ ቢያደርጉ ሕዝብ በብዛት በሚንቀሳቀስበት አካባቢ የእጅ ማስታጠብ በማስፋፋት የቫይረሱን ሥርጭት ለመቀነስ እንደሚያስችል ገልጿል።

የእጅ መታጠብ ባህል እንዲሆን እንፈልጋለን የሚለው የፈጠራ ባለሙያው የእጅ ማስታጠቢያ ወደ ሌሎች አካባቢዎች እንዲስፋፋ የሚመለከታቸው የአካባቢው አካላትና በጎ ፈቃደኞችን ትብብር ባለማድረጋቸው ይወቅሳል።

የአራዳ ክፍለ ከተማም ሆነ የወረዳ 10 የተወሰነ ድጋፍ ቢያደርጉም ከኅብረተሰቡ እንቅስቃሴ አንጻር ግን በቂ አይደለም ሲል ይተቻል።

በአራዳ ክፍለ ከተማ የወረዳ 10 ሥራ አስፈጻሚ አቶ ክብሩ ዱላ በፈጠራ ባለሙያው ታምሩ ካሣ ወቀሳ አይስማሙም።

ሥራአስፈጻሚው አያይዘውም ከበጎ ፈቃደኞች የምናገኘውን ፈሳሽ ሣሙና እያቀረቡ መሆኑንና የእጅ ማስታጠቢያው ዲጂታል በመሆኑ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ከወረዳ 10 ጤና ጣቢያ እንዲያገኝ አድርገናል ብለዋል።

በተጨማሪም በፊት ከነበረው ሦስት ሺህ ሊትር ዉኃ መያዣ ታንከር ወደ 20 ሺህ ሊትር ከፍ እንዲል ማድረጋቸውንም ገልጸዋል።

በማስታጠቡም ወቅት እየተገኙ ሕዝቡ ግንዛቤ እንዲኖረው በማምሸት አብረው እየሰሩ መሆኑን አቶ ክብሩ ገልጸው በሰራው የፈጠራ ሥራ ወረዳውም ሆነ ክፍለ ከተማው በማድነቅ እንዲበረታታ አድርገናል ብለዋል።

ለእጅ ማስታጠቢያ መሣሪያው አስፈላጊው ጥበቃም መድበን እያሰራን ነው የሚሉት ሥራ አስፈጻሚው በአካባቢው የሚገኘውን የኅብረተሰብ ክፍል እንደራሳቸው ንብረት እንዲጠብቁም እያደረግን ነው ብለዋል።

አንዳንድ የኅብረተሰብ ክፍሎች በሰጡት አስተያየት ብዙው የኅብረተሰብ ክፍል ከተለያየ አካባቢ ከትራንስፖርት ስለሚወርደውና ስለሚተላለፈው እንደዚህ ዓይነት ዘመናዊ የእጅ መታጠቢያ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል።

በርካታ የከተማው ሕዝብ በሚንቀሳቀስባቸው አካባቢዎች ከንክኪ ነፃ የሆነ እጅ ማስታጠቢያ ቢስፋፋ የቫይረሱን ሥርጭት ለመቀነስም ያስችላል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም