የሰይጣን ኮሪደር

172

የሰይጣን ኮሪደር —-ከአብዱ ይማም (ኢዜአ)

የጥልቁ ባሕር ምስጢራዊነት የጀመረው በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር ታኅሣሥ 5 ቀን 1945 መሆኑ እርግጥ ነው። በወቅቱ አምስት የአሜሪካ የጦር ጀቶች በበረራ ላይ እያሉ ከጥቂት ቆይታ በኋላ “እምጥ ይግቡ ስምጥ” ሳይታወቅ የውኃ ሽታ ሆነው ቀሩ። የጥልቁ ባሕር ምስጢራዊነት ሳይገለጥ እያነጋገረ በቀጠለበት አጋጣሚ ሌላ በረራ ቁጥር 19 አውሮፕላን ሰማይ ላይ ከታየ ከደቂቃዎች በኋላ ደብዛው ጠፍቶ በሰማይ በምድር ዱካ ሊገኝለት ሳይችል ቀረ።

የዚህ የአውሮፕላን “ሰላቢ ኃይል ማንና የት ነው?” ያለው የሚለው ጉዳይ የህልም ዓለም ሆኖ ሰዓታት ነጎዱ። ጉዳዩ በዝምታ የማይታለፍ አሳሳቢ ክስተት በመሆኑ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞችን የያዘ የቅኝት አውሮፕላን የሰማዩን አድማስ ሰንጥቆ አፍንጫውን ወደ አትላንቲክ ውቅያኖስ በማድረግ ፍለጋውን ቀጠለ።

የነፍስ አድን ሠራተኞችን የያዘው የቅኝት አውሮፕላኑ የተሳካ በረራ ያደረገው ለ20 ደቂቃ ብቻ ነበር። ከዚህ በኋላ ተሰወረ። የአውሮፕላኖች “ቀበኛ” እንዳለ ቢታወቅም፤ ነገር ግን ማንነቱንና ሥፍራውን ማንም እርግጠኛ ሊሆን አልቻለም።

“የገዘፉ አውሮፕላኖችን ምን እየዋጣቸው ነው?” የሚለው ጉዳይ የሰማይም የምድርም ኃይል ያላወቀው ምስጢር ሆኖ ቀጠለ። በአውሮፓውያኑ 1442 በአትላንቲክ ውቅያኖስ በስተሰሜን በኩል ሰማይ ላይ የፈነጠቀው ልዩ ብርሃን ክርስቶፈር ኮሎምበስን በእጅጉ አስደምሞታል። “በሕይወት ዘመኔ አይቼው የማላውቀው የብርሃን ፍንጣቂ የውቅያኖሱን አድማስ ታኮ ይታያል። ነገርዬው የሚያስደምምና የሚያስደንቅ ነው” በማለት ዓለምን በመቃኘት የሚታወቀው አሳሽ ተናገረ። ይህ ጉዳይ ከዘመናት በኋላ ከጠፉት አውሮፕላኖች ጋር ምን ያገናኘዋል ሊያስብል ይችላል። ነገር ግን “ሰኔና ሰኞ” እንደሚባለው ሁሉ፤ “አትላንቲክና የአውሮፕላን መጥፋትም” ቁርኝት ሳይኖራቸው አይቀርም የሚል ጥርጣሬ ማጫሩ ስላልቀረ ነው።

በዚሁ ወቅት ሪቻርድ ውይነር የተባለው ተመራማሪ ባሰፈረው ጽሑፍ “የሰው ልጅ የምድርን ምስጢር በስፋት እየገለጠ ቢሆንም፤ የባሕርና ውቅያኖስን ጓዳ ግን ለማወቅ ብዙ ርምጃዎችን መጓዝ ይጠበቅበታል” ሲል አትቷል። እውነትም አትላንቲክ ያልተገለጡ ምስጢራዊ ጓዳዎች ይኖሩት ይሆን?

በአውሮፓውያኑ መስከረም 8 ቀን 1980 ከጃፓኗ ኦካናዋ ደሴት 150 ሺህ ቶን የብረት ማዕድን ጭና የተንቀሳቀሰችው መርከብ ጉዞዋን ቀጥላለች። መርከቧ ከታይታኒክ በሁለት እጥፍ የምትገዝፍና በወቅቱ ዘመናዊ የተባለች መርከብ እንደነበረችም ይነገርላታል። መርከቧ ሙሉ ሠራተኞቿን (ክሩዋን) እንደያዘች ጥልቁን የአትላንቲክ ውቅያኖስ እየቀዘፈች የአንድ ቀን ጉዞዋን አገባደደች። የሁለተኛ ቀን ጉዞዋን ግን ጀመረችው እንጂ፤ አልጨረሰችም። የእነዚያ ጠፊ አውሮፕላኖች ዕጣ ደረሳትና ግዙፏ መርከብ ተሰውራ ቀረች።

አሁን ጥልቁ የአትላንቲክ ውቅያኖስ በተለይ በሰሜን የባህሩ ክፍል “አንዳች የሚሰውር ነገር ሳይኖር አይቀርም” የሚለው ጥርጣሬና መላ ምት እየተጠናከረ መጥቷል። በዚህ አካባቢ የመርከብና አውሮፕላኖች “ቀበኛ” ሳይኖር እንዳልቀረ የበርካቶች ግምትም ሆነ።

በፈርንጆቹ አቆጣጠር መጋቢት 22 ቀን 1957 የአሜሪካ የጦር አውሮፕላን 67 ወታደሮችን ጭኖ ከቶኪዮ የአውሮፕላን ጣቢያ ተነሳ። የአውሮፕላኑ መዳረሻ የዘጠኝ ሰዓት በረራ እንደሚጠይቅ እርግጥ ነው። ወታደራዊው አውሮፕላን ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖችን ጭኖ ሙሉ የበረራ ዝግጅቱን አጠናቅቋል። በቂ ነዳጅም ሞልቷል።

አውሮፕላኑ ለስምንት ሰዓታት ከሚፈጀው በረራው ለመድረስ የቀረው ከአንድ ሰዓት ያልበለጠ መንገድ ብቻ ነው። የአየር ሁኔታው ለበረራ ምቹ በመሆኑ በተያዘለት ሰዓት መዳረሻው ላይ ለማረፍ መገስገሱን ተያይዞታል። የቶኪዮ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪም የበረራውን ደህንነት እየተከታተለ ይገኛል። ከፓይለቱ ጋር በ200 ማይል ርቀት ላይ ጥርት ያለ የሬዲዮ ግንኙነት እያደረጉ ነበር።

ከደቂቃዎች በኋላ ነገሮች ሁሉ እንዳልነበሩ ሆኑ። 67 ወታደሮችን የያዘው አውሮፕላን በቅጽበት ተሰወረ። የቶኪዮው የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪም ግራ ተጋባ። እውነትም አትላንቲክ መርከብ ከአውሮፕላን እያፈራረቀ በመሰወር “ድብቅ ወንጀለኛ” መሆኑ እየታወቀ መጣ። በአትላንቲክ ውቅያኖስ ሰሜናዊ ክፍል ግዙፍ መርከቦችንና አውሮፕላኖችን እያሰናከለ የሚያስቀር አንዳች ነገር መኖሩም እርግጥ ሆነ። በሰማዩ አድማስ ላይ ኮሎምበስ ልዩ የብርሃን ፍንጣቂ በተመለከተበት አቅጣጫ “ቤርሙዳ ትሪያንግል” የሚባል የሦስት ማዕዘን ቅርጽ ያለው አንዳች ተአምራዊ ነገር እንዳለ ተደረሰበት። እስካሁንም በርካታ መርከቦችና አውሮፕላኖችን ውጦ ያስቀራቸው አደገኛ ሥፍራ ወይም “የሰይጣን ኮሪደር” መሆኑ ተደረሰበት። የዚህ ሥፍራ ምስጢራዊነት ግን ሳይገለጥ የተለያዩ መላምቶች እየተሰጡ እስከ ዛሬም ዘልቋል።

“ቤርሙዳ ትሪያንግል”ን በርካቶች በአዲሰ ሥያሜ ይጠሩት ጀመር። አካባቢው በሰማይና በምድር የሚንቀሳቀሱትን ሕይወት ለመንጠቅ ይቅርታ የለውም። ገዳይ የሆነበት ምስጢር ግን ከመላ ምት የዘለለ የተረጋገጠ ማስረጃ እስካሁን አልቀረበበትም።

ቤርሙዳ ለሰው ልጆች አደገኛ ሥፍራ ተብሎ እስካሁንም በዚሁ ስያሜ ዘልቋል። የጥልቁን ባህር ምስጢር ለማወቅ ተመራማሪዎች ጥረት ከማድረግ ባይቦዝኑም ቤርሙዳ “ውስጤን ለቄስ” ብሎ ቀርቷል።

የጃፓን ባሕር ኃይል የሣይንስና ቴክኖሎጂ ማዕከል በተለያዩ ጊዜያት ባሕር ሰርጓጅ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎችን ወደ ጥልቁ ባሕር ቢልክም፤ 37 ሺህ ጫማ ጥልቀት ያለው ቤርሙዳ እስካሁን ምንነቱን የሚያሳውቅበት መረጃ ሊሰጥ አልቻለም። ምስጢራዊ እንደሆነ ቀጥሏል።

ቤርሙዳ በአሜሪካ ከሚገኘው “ዴዝ ቫሊ”ና በኢትዮጵያ ሰዎች እንዲኖሩበት ከማይመከረው የደንከል ዝቅተኛ ሥፍራ (ዴፕሬሽን) አስፈሪ መሆኑን ብዙዎች ይናገራሉ። በሰዓት 327 ኪሎ ማትር የሚምዘገዘግ አደገኛ ነፋስ ያለበት የአሜሪካው ማውንት ዋሽንግተንም ሰዎች ለመኖር የማይሞክሩበት አደገኛ ሥፍራ ቢሆንም፤ በቤርሙዳ የአየር ክልል ከመብረር ወይም ከመቅዘፍ አይበልጥም የሚሉ በርካቶች ናቸው። እርግጥ ነው የማውንት ዋሽንግተን ቅዝቃዜ በደቂቃዎች ውስጥ ሕይወት ሊቀማ ይችላል። ነፋሱም ቢሆን ተዘናግቶ የቆመን ሰው ድራሹን ለማጥፋት ጉልበቱ አለው። ለሰው ልጆች እጅግ አስፈሪ በመሆን ግን “ማን እንደ ቤርሙዳ” ይላሉ የተፈጥሮ ሣይንስ ተመራማሪዎች።

በብራዚል የሚገኘው የእባብ ደሴት፣ የቦሊቪያው ማዲኒ ብሔራዊ ፓርክም የሰዎችን ሕይወት በሚቀሙ በርካታ ነገሮች የተሞሉ ናቸው። በእነዚህ ሥፍራዎች የሰው ልጅ ከቶውኑም ለደቂቃዎች በሕይወት መኖር አይቻለውም። የኃያላን አገሮች ኒውክሌር መሞከሪያ የሆነውና በርካታ የኒውክሌር አረሮች የሚርመሰመሱበት “ማርሻል ደሴት”ና የታንዛኒያው ናይትሮን ባሕርም ነፍስ ላለው ነገር ሁሉ የሚሳሱ አይደሉም። እነዚህ ሁሉ ሕይወት የሚቀሙበት የየራሳቸው ምክንያት አላቸው። የአትላንቲኩ ቤርሙዳ ግን ሕይወት የመቀማት ምስጢር ሳይገለጥ እልፍ ዓመታት እየነጎዱ ነው።

አምስቱ የአሜሪካ የጦር ጀቶች የተሰወሩትም የዛሬ 75 ዓመት ነበር። ቤርሙዳ እስካሁን ከ50 በላይ ግዙፍ መርከቦችንና ከ20 የሚልቁ አውሮፕላኖችን “የውኃ ሽታ” አድርጓቸው ቀርቷል። ቤርሙዳ ምስጢርህን የምትገልጽበት ጊዜ መቼ ይሆን?